ብቻውን ሮምን የወረረው ወታደር፡- አበበ ቢቂላ

1 Mon Ago 801
ብቻውን ሮምን የወረረው ወታደር፡- አበበ ቢቂላ

የአፍሪካ እና የጥቁር ሕዝብ የይቻላል እና የድል ብስራት ፋና ወጊ፣ በባዶ እግሩ ማራቶንን ሮጦ ያሸነፈ ቆፍጣና የአባቶቹ ልጅ፣ ጣሊያኖች ከኢትዮጵያ ወስደው በሮም አደባባይ በተከሉት የኢትዮጵያውን የሥልጣኔ መገለጫ በሆነው የአክሱም ሀውልት ፊት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓለማ ከፍ ያደረገ፡፡

የኦሎምፒክ ማራቶንን የወቅቱ ክብረ ወሰን ሰብሮ በሮም አደባባይ የደመቀ፣ ከዚያ በፊት ተደርጎ የማያውቀውን ከዚያ በኋላም ለረጅም ጊዜ ሳይሞከር የቆየውን በሁለት ተከታታይ ኦሎምፒኮች የማራቶን የወርቅ ሜዳሊያን ለሀገሩ ያበረከተ፡፡

ሦስተኛ ተከታተይ ኦሎምፒክ ላይም ተሳትፎ ሩጫውን አጋምሶ በህመም ምክንያት አደራውን ለሀገሩ ልጅ አስረክቦ ኢትዮጵያን በሦስት ተከታታይ ኦሎምፒኮች የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ያደረጋት፡፡

ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች የይቻላል እና የድል ወኔን  ያወረሰ የምንጊዜም የኢትዮጵያ ጀግና አበበ ቢቂላ!

ሻምበል አበበ ቢቂላ የተወለደው ነሐሴ 30 ቀን 1925 ዓ.ም ደነባ ልዩ ስሟ ጃቶ ከምትባል ሥፍራ ነው። በልጅነት ዕድሜው ጎበዝ የገና ተጫዋች እንደነበር ይነገርለታል። የክብር ዘበኛ ወታደር ሆኖ ከተቀጠረ በኋላ በተለያዩ ስፖርታዊ ጨዋታዎች መሳተፉን ቀጠለ።

በአሥራ ስድስተኛው የሜልቦርን ኦሊምፒክ ላይ የተሳተፈውን የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የአትሌትክስ ቡድንን ለመቀበል የተደረገውን ሰልፍ የታደመው አበበ አትሌቶቹ የሀገራቸው ስም የተጻፈበትን መለያ ለብሰው ሲመለከት ሀገርን ወክሎ በዓለም አደባባይ መገኘት ያለው ክብር በልቡ ላይ ታተመ፡፡

ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያን ወክሎ በኦሎምፒክ የመሳተፍ ህልሙን ለማሳካት መሥራቱን ቀጠለ፡፡ በክብር ዘበኛ ሠራዊት ካምፕ ውስጥ የሚያደርጋቸውን ልምምዶች እና ውድድሮች ስዊድናዊው አሰልጣኝ ኦኒ ኒስካነን የአበበን ችሎታውን በመገንዘባቸው ከሌሎቹ አትሌቶች ጋር ተቀላቅሎ ልምምድ እንዲሠራ አደረጉት፡፡ አሰልጣኙ ተራራማ በሆኑ ቦታዎች ላይ የመሮጥ እና የሺህ አምስት መቶ ሜትር ተደጋጋሚ የፍጥነት ሩጫ ልምምዶችን እንዲሠሩ ያደርጓቸው ነበር። በዚሁ ወቅትም የክብር ዘበኛ ሠራዊት ባዘጋጀው ውድድር ላይ ተሳትፎ በ5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትሮች ሩጫ ብሔራዊውን ክብረ ወሰን የያዘዙትን ዋሚ ቢራቱን ቀድሞ አጠናቀቀ። እናም ይህ ድል አበበ ለታላቅ ውድድር እንዲታጭ በር ከፈተለት፡፡

በሮም ኦሎምፒክ ላይ ኢትዮጵያን ከወከሉት ተወዳዳሪዎች መካክልም አበበ ቢቂላ አንዱ ሆነ፡፡ ውድድሩ አንድ ወር ሲቀረው ሮም ከተማ ውስጥ ከአጋሩ አበበ ዋቅጅራ ጋር ሲሰለጥኑ ቆዩ፡፡ የሩጫውን መንገድ በጥንቃቄ እያጠኑ ልምምዳቸውን አጠናከሩ፡፡

ለ10 ሺህ ሜትር የተዘጋጁት እና በኦሎምፒኩ ተሳትፈው ውጤት ያመጣሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው ሻለቃ ዋቢ ቢራቱ ለኦሊምፒኩ ዝግጅት በሚያደርጉበት ጊዜ በአንድ ቀን መቶ ኪሎሜትር በመሮጥ በመታመማቸው ከቡድኑ በመውጣታቸው ነው ሁለቱ አበበዎች ብቻ ኢትዮጵያን ወክለው ሮም የተገኙት፡፡

ከአሳልጣኛቸው እና ልዑካን ቡድኑ በስተቀር ማንም የማያውቃቸው እነ አበበ ሊወዳደሩ የተዘጋጁት በወቅቱ ታዋቂ ከነበሩት የሞሮኮው ራህዲ ቤን አብዴ ሰላም፣ የኒውዚላንዱ ባሪ ማጊ፣ የሶቪዬቱ ሕብረቱ ኮንስታንቲን ቮሮብዮቭ እና በወቅቱ የማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤት ከነበረው ሰርጌይ ፖፖቭ እና የብሪታንያ ተወላጅ ዴኒስ ኦጎርማን ጋራ ነበር።

የሞሮኮው ራህዲ ይለብሳል የተባለው የመለያ ቁጥር 26 ነበር፡፡ አበበም ይህን መረጃ ያውቅ ነበር፡፡ ይሁንና ውድድሩ ሲጀመር ራህዲ ቁጥሩን ቀይሮ ተሰለፈ፡፡ በዚህም አበበ አጠገቡ እየሮጠ የነበረውን ራህዲን ሊያውቀው አልቻልም፡፡ አበበ በውድድሩ ላይ ከሃያ እስከ ሠላሳ ኪሎሜትር ላይ ባሳየው ፍጥነት አብዛኛዎቹን ተወዳዳሪዎቹን ጥሎ በመሄዱ አጠገቡ የቀረው ራህዲ ብቻ ሆነ። እሱም አበበን እንደምንም ብሎ ለመቅደም ቢሞክርም ባለመቻሉ ወደ ኋላ ቀረ፡፡ አበበ ከኋላው የተከተሉት እንዳሉ ኮቴ እያዳመጠ ሩጫውን ቀጠለ፤ እየራቀ ሲሄድ ማንም እየተከተለው እንዳልሆነ ተረዳ፡፡ አሰልጣኙ እንደሚሉት አበበ 26 ቁጥር ይለብሳል የተባለው ራዲን እስከሚያገኘው ድረስ ጉልበቱን ለመቆጠብ ፍጥነቱን ያዝ አድርጎ ባይሮጥ ኖሮ ክብረ ወሰኑን በከፍተኛ ደረጃ ያሻሽል ነበር። ሆኖም አበበ ውድድሩን 2:15:16.2 በሆነ ፍጥነት የዓለም ክብረወሰን አጠናቅቆ ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ የመጀመሪያውን የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ አመጣ፡፡ ይህም ከሱ በኋላ ለመጡት የኢትዮጵያ እና ሌሎች አፍሪካ ሀገራት አትሌቶች የዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳትፎ በር ከፈተ ፡፡ የሞሮኮዎቹ ራህዲ እና ባሪ ማጊ አበበን ተከትለው ጨረሱ።

የአበበ የባዶ እግር ተአምር ያስገረማቸው የጣልያን ጋዜጦች፣ "ኢትዮጵያን ለመውረር በሺዎች የሚቆጠሩ የጣሊያን ወታደሮች አስፈልጎ ነበር፤ ኢትዮጵያ ግን አንድ ወታደር ብቻ ልካ ድፍን ሮምን ወረረችው" በማለት ዘገቡ፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሎምፒክ ውድድር አሸንፎ የወርቅ ሜዳሊያ የወሰደ ጥቁር አፍሪካዊ አበበ ቢቂላ ነው። ይህም አጋጣሚ ለብዙ ጥቁር አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ ውድድር እንዲሳተፉ በር ከፍቷል። የአበበ ቢቂላ ዝናም ከአለም ጫፍ እስከ ጫፍ ተዳረሰ።

አበበ ከዚህ ውድድር በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በተመለሰ በሁለት ወሩ በክብር ዘበኛ ሠራዊት ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል መንግሥቱ ንዋይ እና በወንድማቸው ገርማሜ ንዋይ መሪነት የተካሄደው የታኅሳስ 1953 ዓ.ም መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሲከሽፍ፣ የሠራዊቱ አባል የነበረው አበበም ከሌሎች ወታደሮች ጋር በመጠርጠር ለጥቂት ጊዜ ታስሮ ከድርጊቱ ነጻ መሆኑ ሲረጋገጥ ተፈትቷል።

አበበ ግርግሩ ከተረጋጋ በኋላ እስከ 1954 ድረስ በግሪክ፣ በጃፓን እና በቼኮስሎቫኪያ በማራቶን ተወዳድሮ ሁሉምን ወድድሮች አንደኛ በመውጣት አሸንፏል።

ለቶክዮ ኦሎምፒክ ተሳትፎም ሐምሌ 03 ቀን 1956 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ በተካሄደው የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ማጣሪያ ውድድር አበበ፣ ማሞ ወልዴን እና ደምሴ ወልዴን አስከትሎ በማጠናቀቅ የቶኪዮ ትኬቱን ቆረጠ።

18ኛው የቶክዮ ኦሊምፒክ ሊካሄድ አርባ ቀናት ሲቀሩት አበበ ቢቂላ በማራቶን ውድድር ልምምድ ላይ ባጋጠመው ህመም ምክንያት ወደ ሆስፒታል ሲወሰድ ህመሙ ትርፍ አንጀት ሆኖ ተገኘ። ወዲያው ቀዶ ጥገና ተደርጎለት ለጥቂት ቀኖች ካገገመ በኋላ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ ልምምዱን ቀጠለ።

በቀዶ ጥገናው ምክንያትም አበበ ከኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ቡድን ጋር ወደ ቶኪዮ ተጉዞ ይወዳደራል ብሎ ፍፁም ያሰበ ሰው አልነበረም። የፅናት ተምሳሌቱ አበበ ግን ከአርባ አንድ ሀገራት ከተውጣጡ ተወዳዳሪዎች ጋር  በቶኪዮው መድረክ ተሰለፈ።

ውድድሩበተጀመረ አሥራ አምስት ኪሎ ሜትር  እደተሮጠ ከአበበ ጋር ቀሩት የአውስትራሊያው ሮን ክላርክ እና የአየርላንድ ጄምስ ሆጋን ብቻ ነበሩ። አሰልጣኙ የመከሩትን የመሮጫ ታክቲክ በትክክል የተገበረው አበበ ተወዳዳሪዎቹን አንድ በአንድ እያንጠባጠበ ወደ ማጠናቀቂያ ትራክ አመራ።

ወደ ስታዲዮሙ ሲገባ ብቻውን ለነበረው አበበ፣ በስታዲየሙ የተገኘው 70 ሺህ ተመልካች ከፍተኛ አድናቆቱን ገለጸለት። ውድድሩንም የራሱን ክብረ ወሰን በማሻሻል 2፡12፡11.2 አጠናቀቀ።  ከድሉ በኋላም አበበ 42.195 ኪሎ ሜትር የሮጠ ሳይሆን ገና ሊሮጥ እንደሚሰናዳ አትሌት ሰውነት ማሟሟቂያ መሥራቱን ቀጠለ፡፡ ከውድድሩ በኋላ ተጠይቆ ሲመልስም ሌላ አስር ኪሎ ሜትር ጨምሮ የመሮጥ አቅም እንደነበረው ገልጿል።

አበበ ከሮሙ ድሉ አራት ዓመት በኋላ የቶኪዮ ድሉን ሲደግም የኦሊምፒክን ብቻ ሳይሆን የዓለምንም ክብረ ወሰን መስበር ችሏል። ከእርሱ በፊት ማንም ያልፈጸመውን፣ ከእርሱም በኋላ ለ16 ዓመታት ማንም ያላደረገውን የኦሊምፒክ ማራቶን ሁለት ጊዜ አከታትሎ የመውሰድ ገድልንም ፈጽሟል።

የወቅቱ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ዋና ፀሐፊ እና የኦሎምፒክ ቡድኑ መሪ የነበሩት አቶ ይድናቃቸው ተሰማ፡-

"እንደ በረዶ ነጫጭ ጥርስ አብቅሎ፤

ይቆረጣጥማል ሰዓት እንደቆሎ፤" ብለው ተቀኝተውለታል፡፡

የማራቶን ታሪክ ፀሐፊዎች እና ዘጋቢዎች፣ "ወደር የማይገኝለት እውነተኛ የማራቶን ሯጭ ምሳሌ ሲሉ አወድሰውታል፡፡ ለማንኛውም የማራቶን ሩጫ ተወዳዳሪ ምሳሌ የሚሆን፣ ዓለም ካፈራቻቸው ምርጥ የዓለማችን አትሌቶች አንዱ ነው " ሲሉም አሞግሰውታል ፡፡

አበበ ቢቂላ ሁለተኛውን ወርቅ ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሰ የአዲስ አበባ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ የጀግና አቀባበል ካደረገለት በኋላ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ የሻምበልነት ማዕረግ እና አዲስ ቮልስ ዋገን ቢትል ሸልመውታል።

በ1960 ዓ.ም በሜክሲኮ ከተማ የተካሄደው 19ኛው ኦሊምፒክ ውድድር ከመጀመሩ በፊት እግሩ ላይ ጉዳት ደርሶ የነበረ ቢሆንም ከልዑካን ቡድኑ ጋር ወደ ሜክሲኮ አቅንቷል። ኢትዮጵያ አበበን ጨምሮ ሦስት ሯጮችን አሰልፋለች። ማሞ ወልዴ እና ገብሩ መራዊ ከአበበ ጋር የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ለማድረግ የተሰለፉ አትሌቶች ነበሩ። አበበ ውድድሩን ጀምሮ ከፊት ከሚመሩት ጋር እስከ አስራ ሰባተኛው ኪሎሜትር ድረስ ከሮጠ በኋላ የእግሩ ሕመም ስለጠናበት አብሮት ለነበረው ማሞ ወልዴ አደራ ሰጥቶ ውድድሩን አቋረጠ፡፡

ማሞ ወልዴን፣ "አይዞህ ታሸንፋለህ፤ እኔ አልቻልኩም፤ የእግሬ ወለምታ በጣም ተሰምቶኛል፤ ሌላም የማላውቀው ስሜት እየተሰማኝ ነው፤ ስለዚህ አደራዬን ተቀበለኝ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠብቀናል፤ እኔ ስላልቻልኩ አንተ ቀጥል፤ የኢትዮጵያ አምላክ ይከተልህ!" የአበባ ለማሞ ተሰጠ የአደራ መልዕከት ነበር፡፡

በወቅቱ በቦታው የነበረው ጋዜጠኛ ሰለሞን ተሰማ ሁኔታውን ሲገልጽ፣ "የአበበን መውጣት ስሰማ ማሞን ለማበረታታት የጮህኩት ጩኸት ድምፄን ለሦስት ቀናት ያህል ዘግቶት ነበር" ብሏል፡፡ በውድድሩ ገብሩ መራዊ ስድስተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ አደራውን የተቀበለው ማሞ ወልዴ ድል ተቀዳጅቶ ለኢትዮጵያ ሦስተኛውን የማራቶን ወርቅ አስገኘ።

ሻምበል አበበ ቢቂላ በ1961 ዓ.ም በሽልማት የተሰጠችውን ቮልስ ዋገን መኪና ሲነዳ አደጋ ደርሶበት ከወገቡ በታች ጉዳት ደረሰበት። ወደ እንግሊዝ ተልኮ ሕክምና ቢደረግለትም ስብራቱ ባለመዳኑ በተሽከርካሪ ወንበር ላይ ሆኖ ተመለሰ። እነዚያ ዓለምን ያስደነቁ እግሮች መንቀሳቀስ ተሳናቸው።

አደጋው ከደረሰበት በኋላ "መልካም ውጤት የሚያመጡ ሰዎች አሳዛኝ አደጋም ይገጥማቸዋል፤ በእግዚአብሔር ፍቃድ የኦሎምፒክ ማራቶንን ለማሸነፍ በቃሁ፤ እንዲሁም በእግዚአብሔር ፍቃድ የመኪና አደጋ ደረሰብኝ፤ ድሉን እንደተቀበልኩ ሁሉ እንዲሁም መከራውን መቀበል አለብኝ፤ ሁለቱንም የሕይወት ሁኔታዎች ስለሆኑ በፀጋ ተቀብዬ ሕይወቴን በደስታ መኖር ነው ያለብኝ" በማለት ገልጿል።

የፅናት ተምሳሌቱ አቤ በተሽከርካሪ ወንበር ላይ ሆኖም የቀስት ዒላማ ውድድር ላይ በመሳተፍ አሸንፏል፡፡

በ1964 ዓ.ም በተካሄደው 20ኛው የሙኒክ ኦሊምፒክ ውድድር ላይ በልዩ እንግዳነት ተጋብዞ ውድድሩን ተመልክቷል። የማራቶኑን ውድድር ያሸነፈው አሜሪካዊው ፍራንክ ሾርተር ሽልማቱን ከተቀበለ በኋላ በቀጥታ ወደ አበበ ቢቂላ በመሄድ ለሱ ያለውን ፍቅር እና አክብሮት ገልጾለታል።

"ብቻውን ሮምን የወረረው ወታደር” በተወለደ በ41 ዓመቱ ጥቅምት 15 ቀን 1966 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ከተወዳደረባቸው አስራ አምስት የማራቶን ውድድሮች አስራ ሁለቱን በአንደኛነት ያጠናቀቀው ጀግናው፣ የፅናቱ ተምሳሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ በዚያች ዕለት ወደ ማይቀረው ዓለም ተጓዘ።

አቤ "እኔ ዓለም ሁሉ እንዲያውቀው የምፈልገው ሀገሬ ኢትዮጵያ ሁል ጊዜ የምታሸንፈው በቆራጥነት እና በጀግንነት ነው፤ ለምወዳት አገሬ ኢትዮጵያ እና ሕዝቧ የሺህ ዓመት መኩሪያ እና መከበሪያ ታሪክ በእግዚአብሔር ፈቃድ ስለሠራሁ ከእንግዲህ በኋላ የምመኘው ነገር የለም" በማለት ስለ ስኬቱ ተናግሯል፡፡

እሱ እንዳለውም የማይሞት ታሪክ ሠርቶ ለትውልድ ስላስረከበ አነሆ ዛሬም የሱን ፈለግ ተከትለው የሀገራቸውን ሰንደቅ ዓለማ በዓለም አደባባይ ከፍ ያደረጉ ተከታዮችን አፍርቷል፡፡

አበበ ለሠራቸው ገድሎች በርካታ ሽልማቶች እና መታሰቢያዎች ተበርክተውለታል፡፡ አዲስ አበባ እና አዳማ በስሙ የተሰየሙ ስታዲየሞች፣ በአምስተርዳም የአበበ ቢቂላ ጎዳና፣ በጣሊያኗ ላዲስፖሊ ከተማ የእግር መንገድ እና ድልድይ በአበበ ቢቂላ ስም (ፖንቴ አበበ ቢቂላ)፣ በሴኔጋል መዲና ዳካር ወደ “ዴምባ ዲዮፕ” ስታዲየም የሚያስገባው መንገድ በአበበ ቢቂላ ስም የተሰየሙ ናቸው፡፡ ከሮም ኦሎምፒክ በኋላ የአበበን በበዶ እግር መሮጥ የሚያስታውስ ጫማ ተሠርቶ "ቢቂላ" በሚል ስያሜ ለገበያ ቀርቧል፡፡

33ኛውን የፓሪስ ኦሎምፒክ ምክነያት በማድረግ የኦሎምፒክ ስፖርት ሁሌም በኢትዮጵያውያን  አንዲናፈቅ መሰረቱን ያስቀመጠውን ጀግና አትሌት እንዲህ ዘክረነው፡፡ 

ለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top