የገንዘብ ፖሊሲ ሀገራት በብሔራዊ ባንክ አማካኝነት የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዲኖር በማሰብ የገንዘብ አቅርቦት ላይ የሚሰሩበት መንገድ ነው፡፡
በዚህም የብሔራዊ ባንክ ከቀናት በፊት ፖሊሲ-ነክ የወለድ ምጣኔ የሚል የፖሊሲ ተመን እንደሚጠቀም ይፋ አድርጓል፡፡
ሥድስት ነጥቦችን የያዘው አዲሱ የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ፤ በዋናነት ዋጋን ለማረጋጋት በማሰብ የወጣ ስለመሆኑ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ጣሰው ታደሰ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡
ብሔራዊ ባንኩ ከዚህ ቀደም በገንዘብ አቅርቦት ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ እንደነበረው አስታውሰው ፤ አዲሱ ፖሊሲ የወለድ መጠን ላይ በማተኮር ኢኮኖሚው ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን ገንዘብ መቆጣጠርን ታላሚ ያደረገ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የወለድ መጠን የአንድ ሀገር ማዕከላዊ ባንክ የሀገር ውስጥ ባንኮችን ገንዘብ ለማበደር የሚያስከፍልበት መጠን ሲሆን፤ በቀዳሚነት በሀገሪቷ ባለ የገንዘብ አቅርቦት እና ፍላጎት እንሚወሰን ያስረዳሉ፡፡
በሌላ አገላለጽ ብሔራዊ ባንክ የማበደሪያ መጠኑን ከፍ እና ዝቅ በማድረግ ኢኮኖሚውን ሲዘውር ማለት ነው ይላሉ ባለሙያው፡፡
ይህ መጠን እንደ ወቅታዊው የዋጋ ግሽበት ሁኔታ ሊጨምርም ሊቀንስም ይችላል፡፡
ይህም ማለት በሀገሪቱ የወጋ ንረት ሲታይ ግሽበቱን ለማረጋጋት የወለድ መጠኑ ከፍ እንደሚደረግ ጠቅሰው፤ ኢኮኖሚው ተቀዛቅዟል ተብሎ ሲታሰብ ደግሞ የወለድ መጠኑን መቀነስ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ሌላው በፖሊሲው የተቀመጠው የወለድ ምጣኔ 15 በመቶ እንደሆነ ነው፡፡
የወለድ ምጣው አሁን ላይ ያለውን የሀገሪቷን ማክሮ ኢኮኖሚክስ ሁኔታ፣ የዋጋ ግሽት፣ የገንዘብ አቅርቦት እድገት እና ባንኮች የሚሰጡትን ብድር ከግንዛቤ በማስገባት የወጣ መሆኑን ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡
ይህ ሁኔታ ባንኮች የሚያበድሩትን እና ለተገልጋዮች ተቀማጭ የሚሰጡትን የወለድ መጠን እንደማይተምን ይገልፃሉ፡፡
ፖሊሲው ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ እንቅስቃሴ እጥረት ተፈጥሯል ብሎ ሲያምን እና ባንኮች የገንዘብ እጥረት ሲገጥማቸው ከገንዘብ ፖሊሲ ጋር የተያያዘ ጨረታ በማውጣት ወደ ኢኮኖሚው ገንዘብ እንዲገባ የሚያስችለበትን መንገድ እንደፈጠረም ያስረዳሉ፡፡
አክለውም መጠነ ሰፊ የገንዘብ አቅርቦት በመከሰቱ የዋጋ ግሽበት ይጨምራል ተብሎ ሲታመን፤ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ሆኖ ገንዘብ ከኢኮኖሚ እንዲወጣ የሚያደርግበት መንገድ መሆኑንም ነው የገለፁት፡፡
ሌላው የአንድ ቀን የብድር አገልግሎት እና የአንድ ቀን ተቀማጭ አገልግሎትን ማካተቱ ሲሆን፤ ባንኮች የገጠማቸውን የገንዘብ እጥረት እንዲያቃልሉ ወይም ያላቸውን ትርፍ ገንዘብ በተቀመጠው መጠን መሰረት ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚስችል መሆን ያስቀምጣሉ፡፡
ይህም የባንኮችን የገንዘብ ፍሰት አቅም ለማስተካከል የሚረዳ መሆኑ ነው የጠቆሙት ፡፡
ሌሎች በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረቱ እና በባንኮች ግንኙነት መሰረት የሚፈጠሩ የገንዘብ እጥረቶችን ለመፍታት የሚረዱ የግብይት መንገዶች ለምጣኔ ሀብቱ መረጋጋት ጉልህ ሚና እንዳላቸውም ያነሳሉ፡፡
የፖሊሲውን ጠቀሜታ የገለጹት ጣሰው ታደሰ (ዶ/ር)፤ ፖሊሲው የምጣኔ ሀብትን ለመቆጣጠር እና ለማረጋጋት ብቸኛ ሳይሆን አንዱ አስተዋፅኦ አድራጊ መሆኑን በመጥቀስ፤ ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችም ከግምት ውስጥ ሊገቡ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የገንዘብ አቅርቦት ለኢኮኖሚው ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ የሚገልፁት ባለሙያው፤ ዘላቂ ሰላም፣ የግብርና ምርታማነትን፣የውጭ ምንዛሬ እጥረትን መፍታት፣ የአቅርቦት ማነቆዎችን ማስተካከል እንዲሁም በመንግስት በኩል ለሚወጡ ወጪዎች ቅድሚያ ሊያገኙ ለሚገቡ ጉዳዮች ትኩረት መስጠት የፖሊሲውን ውጤታማነት የሚያፋጥኑ ነጥቦች እንደሆኑ ነው የጠቀሱት፡፡
በአፎሚያ ክበበው