የሰውን ምስል ያለፍቃድ መጠቀም በህግ እንደሚያስቀጣ ያውቃሉ?

5 Mons Ago 1074
የሰውን ምስል ያለፍቃድ መጠቀም በህግ እንደሚያስቀጣ ያውቃሉ?

የዘመኑ ስልጣኔ ካቀለላቸው በርካታ ነገሮች አንዱ ፎቶ ማንሳትና ቪዲዮ መቅረፅ ነው።

የማንኛውንም ሰው ምስል ማግኘትም ሆነ በአንድ ጠቅታ በማህበራዊ ድረ ገፆችና በሌሎች መገናኛ ብዙኃን ማሰራጨቱም ፎቶ የማንሳቱን ወይም ቪዲዮ የመቅረፁን ያህል ቀላል ሆኗል።

የሚዲያው ዓይነት መስፋቱና ወደ ታዳሚዎች የሚደርስበት ሁኔታ እየበዛ መሄዱ፣ በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት በቢሊዮኖች የሚቆጠር የዓለማችን ሕዝብ መልዕክትና መረጃ በቀላሉ መለዋወጥ የሚቻልበት ሥርዓት መፈጠሩ የሰዎችን ፎቶግራፍና ምስል በስፋት መለጠፍና ማሳየት እንዲጨምር አድርጎታል፡፡

ጋዜጣው፣ መጽሔቱ፣ ቴሌቪዥኑ፣ ፌስቡክና ዩቲዩቡ፣ ፊልምና የሙዚቃ ሥራዎች ጭምር ሥርዓት በሌለው መልኩ የሰዎችን ምስል ለሕዝብ በማሳየት የግላዊ ነፃነትን (ግላዊነትን) የሚጻረሩ ድርጊቶች አፋጻጸም ሕጋዊ እስኪመስል ድረስ ተንሰራፍቷል፡፡

ለመሆኑ በሃገሪቱ ህግ መሰረት ግለሰቦች በፎቷቸው ወይም በቪዲዮቻቸው ላይ ያላቸው መብት ከህግ አንጻር እንዴት ይታያል?  የግለሰቦች ፎቶግራፍ ወይም ሥዕል የግላዊ ነጻነት ወይም መብት አካል እንደመሆኑ ግለሰቦቹ በፎቷቸው ላይ ያላቸው መብት እስከ ምን ድረስ ነው?

በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በሚሰራጩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ላይ የሚካተቱ የሌሎች ሰዎች ምስሎችን በተመለከተ ባለምስሎቹ ፍቃዳቸውን ተጠይቀው ያውቁ ይሆን?

ካለ ፍቃድ ምስላቸውን መጠቀም የሚቻልበት ሁኔታዎችስ የትኞቹ ናቸው?

ከነዚህ ሁኔታዎች ውጭ ምስልን ያለፍቃድ መጠቀም ሚያስከትለው የፍትሐ ብሔር ኃላፊነት ምን መሆኑን የሚያሳዩ ሁለት ሙግቶችን እነሆ፦

1.የሕፃኑ ፎቶ

የሕፃን ሪያን ፎቶ የማረከውና ለምርቶቹ ማስታወቂያ ተስማሚ ሆኖ ያገኘው አንድ የኤሌክትሪክ ኬብል (ሽቦ) አምራች ድርጅት ከሰኔ ወር 2000 ዓ.ም ጀምሮ የሪያንን ፎቶ ለማስታወቂያ መጠቀሙን ተያያዘው።

በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ከሰቀላቸው ግዙፍ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች በተጨማሪም በግብፅ እና በሌሎች ሀያ አራት አገራት በበይነ-መረብ ድርጅቱንና ምርቶቹን የሚያስተዋውቁ የሕፃን ሪያን ፎቶ ያለባቸው ማስታወቂያዎች ለእይታ በቁ።

ከሰኔ ወር 2000 ዓ.ም እስከ የካቲት 2004 ዓ.ም ድርጅቱ በሕፃን ሪያን ፎቶ ምርቶቹን ሲያሰተዋውቅ ቆየ። ድርጅቱ ይህን ሲያደርግ ግን የማንንም ፍቃድ አልጠየቀም ነበር።

ይህን ያወቀችው የሕፃን ሪያን ሞግዚት (ማለትም 18 ዓመት ስላልሞላው መብቶቹን በተመለከተ እንድትወክለው በሕግ እውቅና የተሰጣት) ወ/ሮ ፋጡማ ይህን ድርጅት ካሳ ክፈለኝ ካለፍቃዴ የሕፃኑን ፎቶ ለማስታወቂያ ተጠቅመሀል ብላ ጠየቀችው። ድርጅቱም በሽምግልና 15,000 ብር ካሳ ሊከፍል ተስማማ።

የሕፃን ሪያን ሞግዚት ግን በማስታወቂያው ከተገኘው ጥቅም ጋር ሲነፃፀር ካሳው ተመጣጣኝ አይደለም አልቀበልም ብላ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 400 ሺህ ብር ካሳ እንዲከፈላት ከሰሰች።

ምን ትላላችሁ ክሱ ያዋጣታል? ውሳኔውን ከማንበባችሁ በፊት የራሳችሁን ግምት ስጡና ግምታችሁን በአስተያየት መስጫው ውስጥ አጋሩን።

2.የደንበኛውን የቪዲዮ ምስል የተጠቀመው ባንክ

ባንኮች የመገናኛ ብዙኃንን አገልግሎታቸውን ለማስተዋወቅ አብዝተው ከሚጠቀሙ ተቋማት ግንባር ቀደሞቹ ናቸው። አንድ ባንክም አገልግሎቱን በ2006 ዓ.ም በነበረው የብራዚሉ ዓለም ዋንጫ ላይ በቴሌቪዥን ሲያስተዋውቅ አንድ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ደንበኛውን የባንኩን አገልግሎት ከባለቤታቸው ጋር ሲጠቀሙና ተጠቅመው ሲወጡ የሚያሳይ ምስል ያለፍቃዳቸው ተጠቅሞ በቀን ከ2 እስከ 3 ጊዜ በኢትዮጽያ ቴሌቪዥን በማስተላለፉ ባለምስሉ 400 ሺህ ብር ካሳ እንዲከፈላቸው ክስ አቀረቡበት።

ባንኩም ለክሱ በሰጠው መልስ ከአንድ ሰከንድ ያነሰ የከሳሽን ምስል የባንኩን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ሲያሳይ መጠቀሙንና በዚህም ከሳሽ ላይ የደረሰ ጉዳት ካለመኖሩም በላይ ተከሳሽም የከሳሽን ምስል በመጠቀሙ ያገኘው ጥቅም ባለመኖሩና ከሳሽም ይህን በማስረጃ ባለማስረዳታቸው እንዲሁም ድርጊቱን ከማስቆም ውጭ ካሳ ሊጠይቁ የሚችሉበት የሕግ አግባብ ስለሌለ ክሱ ውድቅ ይደረግልኝ ሲል መልስ ሰጠ።

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም ምስሉ አጭር ከመሆኑም በላይ የባንኩ የሥራ እንቅስቃሴ ላይ እንጂ ከሳሽ ላይ ያተኮረ ባለመሆኑ ባንኩ አመልካች ላይ ያደረሰው ጉዳት የለም በሚል ክሱን ውድቅ አደረገው።

ከሳሽ ጉዳያቸውን በይግባኝ ወደ ፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ወሰዱት ከፍተኛው ፍ/ቤትም ባንኩ ከሳሽ የውጭ ዜጋ መሆናቸውን በመጠቀም የውጭ ሀገር ባንኮችን የክፍያ ካርዶች በሀገር ውስጥ እንደሚቀበል ለማስተዋወቅ ያለፍቃዳቸው በመጠቀሙ የ 100 ሺህ ብር ካሳ እንዲከፍላቸው ወሰነ።

ከሳሽም ካሳው እንሷል ወይም የካሳው መጠን የተወሰነበት አግባብ ላይ የሕግ ስህተት ትፈፅሟል ሲሉ ለፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ አቀረቡ።

ምን ሚወሰንላቸው ይመስላችኋል?

  1. የሰበር ውሳኔዎች

የሕፃን ሪያን ጉዳይን በተመለከተ ፍ/ቤቱ የተከሳሹን የኤሌትሪክ ሽቦ አምራች ድርጅት መከራከሪያ ከሰማ በኋላ ካለ ሞግዚቷ ፍቃድ የሕፃን ሪያንን ፎቶ ለማስታወቂያ በመጠቀሙ ሁለት መቶ ሺ ብር ካሳ እንዲከፍል ወሰነበት።

ከሳሽም ሆነች ተከሳሽ በውሳኔው ቅር ተሰኙ። በመሆኑም የሕፃን ሪያን ሞግዚት ካሳው አንሶኛል ስትል፤ ተከሳሹ ደግሞ በዝቶብኛል ሲሉ ለከፍተኛው ፍ⁄ቤት ይግባኝ አቀረቡ። ፍ/ቤቱ የከሳሽን ይግባኝ ባይቀበላትም ለተከሳሽ የካሳውን መጠን 150 ሺህ ይበቃታል ብሎ 50 ሺህ ብር ቀንሶ ወሰነለት።

የሕፃን ሪያን ሞግዚት ወ/ሮ ፋጡማም የሕግ ስህተት ተፈፅሟል 400 ሺህ ጠይቄ 150ሺ ብር ብቻ መወሰኑ አግባብ አይደለም ይታረምልኝ ብላ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አመለከተች።

አምስቱ የሰበር ዳኞች ክርክሩን መርምረው አራቱ 150 ሺ ብር ካሳ በቂ ነው ብለው በድምፅ ብልጫ ተወሰነ። አንዱ ዳኛ በሀሳብ ተለይተው ሕፃናት በተፈጥሯቸው ሳቢ ከመሆናቸውና ከማስታወቂያው ስርጭት ስፋት አንፃር 200 ሺህ ብር ይገባታል አሉ።

የባንኩና ካለፍቃዳቸው የቪዲዮ ምስላቸው ለማስታወቂያ በቴሌቪዥን የተሰራጨባቸው ከሳሽ ክርክርም በሰበር ውሳኔዎች ቅፅ 23 ላይ በታተመውና ሕዳር 14 ቀን 2011 ዓ.ም በዋለው ችሎት ላይ በተሰጠው ውሳኔ ከሳሽ ያለፍቃዳቸው የቪዲዮ ምስላቸው በመሰራጨቱ  100 ሺህ ብር ይከፈላቸው ሲል ከፍተኛው ፍ/ቤት የሰጠውን ውሳኔ አፅንቶታል።

4.የውሳኔዎቹ መሰረቶች

ለውሳኔዎቹ መነሻ የሆነው የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁ.27 መሰረት፤ ባለ ፎቶግራፉ ወይም ባለ ስዕሉ ካልፈቀደ የማንም ሰው ፎቶግራፍ ወይም ስዕል በሕዝብ አደባባይ ሊለጠፍም ሆነ ሊባዛ ወይም ሊሸጥ አይችልም የሚለው ድንጋጌ አለው።

ሆኖም ምስሉ የታዋቂ ሰው በመሆኑ፣ በሚሠራው ሕዝባዊ ሥራ፣ በፍርድ ቤትና በፖሊስ አስፈላጊ በመሆኑ፣ ለኪነ ጥበብ፣ ለሳይንስ፣ ለስልጣኔ፣ ለትምህርት መስጫ ወይም ምስሉ የተወሰደው በክብረ በዓል ወይም በሕዝብ ስብሰባ ላይ ከሆነ የባለ ምስሉ ፍቃድ አያስፈልግም ሲል ይደነግጋል።

ከነዚህ ሁኔታዎች ውጭ ምስሉ ካለ ፍቃዱ በአጥር፣ በየመንገዱ በተገኘው ቋሚ ነገር ላይ፣ በቲሸርት ላይ፣ በማህበራዊ ድረ ገፅ ግድግዳ ላይ ወይም በመሳሰሉት ባደባባይ የተለጠፈበት ወይም የተሰራጨበት፣ ለሽያጭ ወይም ለማስታወቂያ የቀረበበት ሰው በፍ⁄ብ⁄ሕ/ቁ 29 መሰረት ድርጊቱ እንዲቆም በሕግ የማስገደድ መብት አለው።

ምስሉ ለአደባባይ በመዋሉ የተገኘ የገንዘብ ጥቅም ካለ ጥቅሙን ያገኘው ሰው ተመጣጣኝ ካሳ ለባለ ምስሉ እንዲከፍል ዳኞች መወሰን ይችላሉ። ባለምስሉ በሕይወት ከሌለ ወይም ፍቃዱን መስጠት ካልቻለ ማለትም (በአእምሮ ሕመም ወይም ለአካለ መጠን ባለመድረሱ) ድርጊቱ የባለምስሉን ክብር የሚነካ ሆኖ ካገኙት የቅርብ ቤተ ዘመዶቹ ከላይ የተጠቀሱትን የባለምስሉን መብቶች ተግባራዊ ማድረግ ይችላሉ።

ስንቋጨው የሌላ ሰውን ተንቀሳቃሽ ምስል ወይም ፎቶ ለተለያዩ ተግባራት ስንጠቀም፣ ስንለጥፍም ሆነ ስናሰራጭ ካለፍቃድ መጠቀም የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች፣ ከነዛ ሁኔታዎች ውጭ ከሆነ ፍቃድ ማግኘታችንን ማረጋገጥና ያን አለማድረጉ ሊያስከትል የሚችላቸውን ኃላፊነቶችን ማገናዘቡ ይመከራል።

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top