ትኩረት የተሰጠው የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች (ስቶክ) ገበያ ምንድን ነው?

1 Mon Ago 1057
ትኩረት የተሰጠው የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች (ስቶክ) ገበያ ምንድን ነው?

የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ማለት የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ሽያጭ፣ ግዥ እና ልውውጥ በቋሚነት የሚደረግበት ቦታ ሲሆን፤ የዘርፉ ምሁራን ለተቋማት የገንዘብ ምንጭ እና ማደግ፣ ለሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት (ጂዲፒ) መጨመር፣ ለተሳለጠ የግብይት ስርዓት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያደርግ ነው ሲሉ ይገልፁታል። 

ገበያው በመሰረታዊነት በሁለት የሚከፈል ሲሆን፤ የመጀመሪያ ደረጃ ገበያ እና ሁለተኛ ደረጃ ገበያ በመባል ይታወቃል። 

የመጀመሪያ ደረጃ ገበያ ማለት በውክልና ሻጮች አስተባባሪነት የአዳዲስ አክሲዮኖች፣ ቦንድ፣ የተስፋ ሰነዶች እና ሌሎች ገንዘባዊ ሰነዶችን በመሸጥ አዲስ ካፒታል የሚሰበሰብበት ገበያ ሲሆን፤ ሁለተኛ ደረጃ ገበያ ኢንቨስተሮች በመጀመሪያ ደረጃ አስቀድመው የወጡ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን ከሌሎች ኢንቨስተሮች የሚገዙበት ገበያ ማለት ነው። 

በሀገራችን በ1950ዎቹ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአዲስ አበባ የአክሲዮን መሸጫ ማህበር (Addis Ababa Share Dealing Group) በሚል የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በማቋቋም የተለያዩ አክሲዮኖችን ይሸጥ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል። 

ከዚያ ወቅት ጀምሮ ትኩረት ሳያገኝ እና ሲቀዛቀዝ ለቆየው ዘርፍ የፌዴራል መንግሥት የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አዋጅ ቁጥር 1248/2013 አፅድቆ ስራ ላይ አውሏል፤ በአዋጁ መሰረትም የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ አቋቁሟል። 

በዚህም በካፒታል ገበያ አዋጁ በተደነገገው መሠረት በ25 በመቶ የመንግስት ባለቤትነትና በ75 በመቶ የግሉ ዘርፍ ባለቤትነት ተቋቁሟል። 

በኢትዮጵያ የተማከለና መደበኛ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ያልነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የተጠና የገበያ ምህዳር እየተቋቋመ ነው የሚሉት በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ከፍተኛ የተግባቦት እና የትብብር ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ወንጌል ታመነ ናቸው። 

የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጭዎች፣ ኢንቨስተሮች፣ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ አውጭዎች፣ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ፣ ተገቢነት ያላቸውን ውሎች ያደረጉ ብቁ የሆኑ ተጓዳኝ ወገኖች፣ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች አስቀማጭ፣ ክፍያ አጣሪ እና ፈፃሚ ኩባንያዎች የዘርፉ ተዋናዮች መሆናቸውን ሥራ አስኪያጇ ይናገራሉ። 

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የተለያዩ ሃላፊነቶች እንዳሉበት የሚገልፁት ወንጌል፤ ዘርፉ ፍትሃዊ፣ ግልፅ፣ ሁሉም ተሳታፊዎች ከኤሌክትሮኒክ መገበያያ ዘዴው ጋር የተሳሰሩ እና የኢንቨስተሮች ጥበቃ ቁጥጥር ማዕቀፍ የተከበረበት እንዲሆን ገበያውን እና አባላቱን በቅርበት በመከታተል በመስኩ ተዓማኒነት እንዲረጋገጥ እንደሚሰራ ይገልፃሉ። 

መስኩ የተለያዩ ግብዓቶች እንዳሉት በመናገር ደላላዎች፣ የኢንቨስትመንት ባንኮች፣ የኢንቨስትመንት አማካሪ ድርጅቶች፣ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ አከናዋኝ (securities dealer)፣ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ አስቀማጭ እና ክፍያ አጣሪ እንዲሁም ፈፃሚ ኩባንያ እና ሌሎች በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ፍቃድ የተሰጣቸው የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን እንደሚያካትት ያስረዳሉ። 

ገበያው በአንድ ሃገር የምጣኔ ሃብት እና ጠቅላላ የሃገር ውስጥ ምርት ላይ የሚያሳድረው አዎንታዊ ተፅዕኖ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን የሚገልፁት ሥራ አስኪያጇ፤ ገበያው ከገንዘብ ገበያ ጋር ሲነፃፀር ለረጅም ጊዜ የሚጠቅም ካፒታል የሚገኝበት ምንጭ ነው ሲሉ ያስቀምጣሉ። 

ይህም ድርጅቶችን በካፒታል ገበያ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ በማስቻል ለረጅም ጊዜ ሊቆይ የሚችል ከፍተኛ የሆነ ሃብት ለመሰብሰብ መንገድ በመክፈት፣ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳታፊ የሚሆኑበትን እድል በማመቻቸት የሃገር ምጣኔ ሃብት ግንባታ ላይ የራሳቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ያስችላል ይላሉ። 

ከዚህም ባለፈ ኢንቨስት የማድረግ አቅም ያላቸው ግለሰቦች እና ተቋማት የሚገናኙበትን መድረክ በማመቻቸት እና የካፒታል ተደራሽነትን በማሳለጥ፣ ኩባንያዎች ከማህበረሰቡ ገንዘብ የሚያሰባስቡበት መንገድ በማመቻቸት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ፣ በምርምር እና በተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ መንገዶችን በማመቻቸት ከፍተኛ አዎንታዊ ሚና ይጫወታሉ ሲሉ ይጠቅሳሉ። 

አያይዘውም ቀልጣፋ በሆነ መንገድ ፈጠራን በማበረታታት የንግድ ተቋማት የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴያቸውን እንዲያሻሽሉ፣ አዳዲስ ምርቶችን እና ቴክኖሎጂዎችን እንዲያዳብሩ፣ ተለዋዋጭ ከሆነው ዓለም አቀፋዊ አስተሳሰብ ጋር አብረው እንዲራመዱ፣ ተለዋዋጭ የገበያ ሁኔታዎችን በመመልከት ተወዳዳሪ ሆነው እንዲቀርቡ እድሉን በማመቻቸት፣ ከንግድ ድርጅቶች መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚመጣን የስራ እድል ፈጠራ እና ስራ ፈጣሪነትን በማበረታታት ለአንድ ሃገር የምጣኔ ሃብት ዕድገት ከፍተኛ የሆነ ጠቀሜታ እንዳለው ያስረዳሉ። 

አክለውም በሀገራችን የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያዎች ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልግ አካልን የኢንቨስትመንት ምንጭ ከሚፈልግ ወገን ጋር በተደራጀ፣ ተገቢው የሕግ ጥበቃ በሚደረግለት መንገድ አንድ ቦታ ላይ በማገናኘት የመቆጠብ ባህልን እና ኢንቨስት የማድረግ ልምድን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያበረታታ አስተማማኝ የምጣኔ ሃብት መሳሪያ ነው ሲሉ ያስረዳሉ። 

በአፎሚያ ክበበው


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top