በምሥራቅ ጎጃም ዞን ባሶ ሊበን ወረዳ 12 ሺህ ሄክታር መሬትን በአንድ ጀንበር በስንዴ ዘር ለመሸፈን እየተሠራ ነው

1 Mon Ago 308
በምሥራቅ ጎጃም ዞን ባሶ ሊበን ወረዳ 12 ሺህ ሄክታር መሬትን በአንድ ጀንበር በስንዴ ዘር ለመሸፈን እየተሠራ ነው

በምሥራቅ ጎጃም ዞን ባሶ ሊበን ወረዳ ዞናዊ የ2016/2017 የመኸር ምርት ዘመን የስንዴ ሰብል የኩታ ገጠም የዘር ማስጀመሪያ መርሃ ግብር እያካሄደ ነው።

በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የተገኙት የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ዋለ አባተ ዞኑ በክልልም ሆነ በሀገር ደረጃ ትርፍ አምራች መሆኑን ገልጸው፣ በተለይም ስንዴ እና ጤፍን በሰፊዉ በማምረት የሚታወቅ ስለመሆኑ አንስተዋል።

መንግሥት አርሶ አደሩ ባለፈው ዓመት አጋጥሞት የነበረውን የግብዓት በተለይም የማዳበሪያ እጥረት በመቅረፍ፣ በዚህ ዓመት በሙሉ አቅሙ እንዲያለማ ለማስቻል ማዳበሪያ እና ሌሎች የግብርና ግብዓቶች ፍትሃዊ በሆነ እና በበቂ ሁኔታ እንዲደርስ ማድረጉን ምክትል አስተዳዳሪው ገልጸዋል።  

አርሶ አደሩ የሰፈነውን ሰላም በመጠቀም በሙሉ አቅሙ ወደ ማምረት ተግባር ገብቷል ያሉት አቶ ዋለ፣  የዞኑ አርሶ አደሮች ስንዴን በስፋት በማምረት ሀገሪቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያስቀመጠችውን ግብ ለማሳካት በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ መኮንን በበኩላቸው፣ በ 2016/2017 ዓ.ም የመኸር ምርት ዘመን ከ612 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በዘር በመሸፈን ከ23.3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በመኸር ምርት ዘመኑ የግብርና ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የኩታ ገጠም አሠራር በስፋት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት መምሪያ ኃላፊው፣ በዞኑ 223 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል የሚሸፈን 10 ሚሊዮን ኩንታል ለማግኘት መታቀዱን ገልጸዋል። 

ከዚህ ውስጥ 163 ሺህ ሄክታሩን መሬት በኩታ ገጠም አሠራር በዘር በመሸፈን 8 ሚሊዮን ኩንታል ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዞኑ በምርት ዘመኑ በዘር ከሚሸፈነው አጠቃላይ ማሳ ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ እና ሌሎች ሰብሎች 460 ሺህ ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም አሠራር እንደሚሸፈን በመግለጽ፣ በዚህም 16.9 ሚሊዮን ኩንታል ለማግኘት መታቀዱን ነው የተናገሩት።

ማሳቸውን በኩታ ገጠም አሠራር በስንዴ ሰብል እየሸፈኑ የሚገኙ በባሶሊበን ወረዳ የልምጭም ቀበሌ ነዋሪዎች በበኩላቸው፣ ሰብላቸውን በኩታ ገጠም ዘዴ መዝራታቸው ለአሰሳ ሥራ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠሩ በተጨማሪ በምርት ጭማሪ ላይ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው መናገራቸውን ከምስራቅ ጎጃም ዞን ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top