የሕዝብ ችግር መፍታት የሚችሉ የተለያዩ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሥርዓቶችን መጠቀም ይገባል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

1 Mon Ago 233
የሕዝብ ችግር መፍታት የሚችሉ የተለያዩ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሥርዓቶችን መጠቀም ይገባል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

የሕዝብ ችግር መፍታት የሚችሉ የተለያዩ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሥርዓቶችን አበልፅጎ መጠቀም እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ተቀማጭነቱን ባደረገው ፕሪሳይት በተባለው ተቋም ለሦስት ቀናት በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ዙሪያ በተዘጋጀው ዐውደ ጥናት ላይ ተካፍለዋል፡፡

ዐውደጥናቱ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች የተገኙበት እና በቢግ ዳታ፣ ጄኔሬቲቭ ኤ.አይ፣ በአመራሮች ውሳኔ አሰጣጥ፣ በፖሊሲ እና ሕዝብን በማገልገል ሂደት ውስጥ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ውጤታማነትን እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል ግንዛቤ የተወሰደበት እንደነበር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዛሬ ላይ በሁሉም መስኮች አገልግሎት ላይ እየዋለ ነው ያሉት  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በመንግሥት አሰራሮች፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በንግድ፣ በትምህርት እና ሌሎችም መስኮች መሠረታዊ ለውጥ እያመጣ ይገኛል ብለዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ፤ እኛም በዚህ ዘርፍ በርትተን በመስራት እና የሕዝባችንን ችግሮች መፍታት የሚችሉ የተለያዩ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሥርዓቶችን በማበልፀግ መጠቀም ይገባናል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

የቴክኖሎጂውን ሙሉ አቅም ተገንዝቦ ወደተግባር የሚለውጥ የሰው ኃይል መገንባት ሌላኛው ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ 

ከዚህ አንጻር እንደነዚህ ያሉ ዐውደ ጥናቶች ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡

በወዳጅ ሀገር የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ተቀማጭነቱን ባደረገው ፕሪሳይት በተባለው ተቋም ለሦስት ቀናት የተዘጋጀው ዐውደ ጥናት በዘርፉ ያቀድነውን ወደመሬት ለማውረድ ከሚሰጠው አቅጣጫ አንጻር ስኬታማ ነበር ሲሉም ገልፀዋል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top