የሶማሌ ክልሏ ዳራቶሌ ከተማ የሶላር ሀይል ተጠቃሚ ሆነች

1 Mon Ago 335
የሶማሌ ክልሏ ዳራቶሌ ከተማ የሶላር ሀይል ተጠቃሚ ሆነች

በሶማሌ ክልል ዳራቶሌ ከተማ 90 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የተገነባ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጅምሯል።

የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሡልጣን ወሊ (ዶ/ር ኢ/ር) ፕሮጀክቱን መርቀው ሥራ ያስጀመሩ ሲሆን፣ 725 ኪሎ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳለው በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ገልፀዋል።

እንደ ሀገር በ2030 የተቀመጠውን ሁሉንም ማህበረሰብ የሀይል ተጠቃሚ የማድረግ እቅድ የሚተገበረው ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ርቀው የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን በሶላር ሀይል በማድረስ መሆኑን ሚኒስትር ደኤታው ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ አምስት አመታትም ከልማት ባንክ በተገኘ ድጋፍ 300 የሶላር ሀይል ማመንጫዎች ይገነባሉ ማለታቸውን ከውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ዳራቶሌ ከተማ ከዋናው ኤሌክትሪክ መስመር በ200 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኝ ሲሆን፤ የሶላር ሀይል ተጠቃሚ ከሆኑ 25 ከተሞች አንዷ መሆን ችላለች።

ፕሮጀክቱ እስከ 2 ሺ 500 የሚደርሱ አባዎራዎችን የኃይል ተጠቃሚ ማድረግ እንዲችል ታሳቢ ተደርጎ የተገነባ ሲሆን፤ አገልግሎቱ ለአካባቢው ማህበረሰብ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያው እንቅስቃሴ የኃይል አቅርቦት የሚሰጥ ነው ተብሏል፡፡

በአጠቃላይም 15 ሺህ 500 ለሚሆኑ ዜጎች የኃይል አቅርቦት መስጠት እንደሚያስችል ተጠቅሷል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top