ቤቲ ብሩስል በ3 የዋና ውድድር አይነቶች የ400 ሜትር ነፃ ቀዘፋ ፣ 50 ሜትር የጀርባ ቀዘፋ እንዲሁም በ50 ሜትር የደረት ቀዘፋ አዲስ የዓለም ሪከርዶችን በማስመዝገብ ስማቸው በክብር የተጻፈላቸው ሆነዋል።
በስልሳዎቹ አጋማሽ ላይ የዋና ውድድር ስፖርት ላይ መሳተፍ የጀመሩት እኚህ ሴት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሜዳሊያዎችንም ያገኙ ባለታሪክ ናቸው።
በእርሳቸው እድሜ 400 ሜትር ነፃ ቀዘፋን በ12 ደቂቃ ከ50 ሰከንድ፣ በ50 ሜትር የጀርባ ቀዘፋ ደግሞ በ1 ደቂቃ ከ52 ሰከንድ እንዲሁም 50 ሜትር የጀርባ ቀዘፋን በ1 ደቂቃ ከ24 ሰከንድ በማጠናቀቅ ነው የዓለም ሪከርድ ባለቤት መሆን የቻሉት ብሏል ዋሽንግተን ፖስት።
በኔዘርላንድ ያደጉት ብሩስል እንደ ዋና እና ጅምናስቲክ ያሉ ስፖርቶችን የሚወዱ ቢሆንም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ታናናሽ ወንድም እህቶቻቸውን የመንከባከብ ሃላፊነት ምክንያት ከሚወዱት ስፖርት እንዲርቁ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።
ብሩስል በአውሮፓውያኑ 1959 አሁን ወደ ሚኖሩበት ካናዳ ከገቡ በኋላ ልጆቻቸውን ከማሳደግ በተጨማሪ የጽዳት ስራን በመስራት በኋላም በልብስ ስፌት ስራ መተዳደር መጀመራቸውን የኋላ ታሪካቸው ያስረዳል።
በ1982 ብሩስል ጡረታ ሲወጡ ግን ባገኙት ጊዜ በልጅነታቸው ይወዱት ወደነበረው የዋና ስፖርት ለመመልሰ እድል በማግኘታቸው በ1991 የመጀመሪያ የዋና ውድድራቸውን አደረጉ።
ያን ጊዜ ብሩስል ሲያስታውሱ "የአንድ መስመር የደረት ቀዘፋን ዋኘሁ፣ እና በትክክል እንኳን አላደረግኩትም" ብለዋል።
“በዓላማ እና በፍጥነት ትሄዳለች ፣ ብሩስል እንደ 99 ዓመት ሴት አይደለችም። ደሞም ብሩሰል በዚህ ውድድር ላይ ምን ያህል የዓለም ሪኮርዶች እንዳስቀመጠች እርግጠኛ አይደለችም፣ ምክንያቱም እሷ ይሄን አትከታተልም።” በማለት ዋና አሰልጣኛቸው ሊንዳ ስታንሊ ተናግረዋል።
ዛሬ ላይ ታዲያ 100 ለዓመት ለመሙላት ወራት የቀሯቸው እኚህ አዛውንት ሪከርዶችን በመስበር አዳዲስ ታሪኮችን የሚጽፉ ሰው ሆነው ስማቸው በተደጋጋሚ የሚነሳ ሆኗል።