የረቂቅ ሙዚቃ እስፔሻሊስቱ - ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ

7 Mons Ago 1542
የረቂቅ ሙዚቃ እስፔሻሊስቱ - ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ

የመጀመርያውን የረቂቅ ሙዚቃ ትምህርት ተምረው ከመጡት ውስጥ ግንባር ቀደሙ ሰው፣ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ትምህርት ታሪክ ማስጀመርያ መሰረት ይሏቸዋል የዘርፉ ምሁራን።

የረቂቅ ሙዚቃው ሊቅ ትልቁን የኢትዮጵያ ሙዚቃ ትምህርት ቤት የሆነውን ያሬድ የሙዚቃ ት/ቤት በማቋቋም እና በዳይሬክተርነት በመምራት ስማቸው በጉልህ የሚነሳ፣ የባለዋሽንቱ እረኛ ሙዚቃ ፈጣሪ፡፡

ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ የተወለዱት ግንቦት 8 ቀን 1930 ዓ.ም ነው። አባታቸው ግራዝማች ከበደ አድነው ሲሆኑ  የሙዚቃ ፍቅር ከልጅነታቸው ጀምሮ  እንዲያድርባቸው ያደረጓቸው ደግሞ እናታቸው ወ/ሮ ፈንታዬ ነከሬ መሆናቸው ይነገራል።

መሰረታዊ የሚባለውን ትምህርታቸውን በዳግማዊ ምኒሊክ ት/ቤት እና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ 2ተኛ ደረጃ ት/ቤት (የአሁኑ ኮከብ ጽባሕ) ካጠናቀቁ በኋላ ከሐረር የመምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጅ በመምህርነት ተመርቀዋል።

ከፍተኛ ትምህርታቸውን ደግሞ በኒው ዮርክ ከሚገኘው የሮቼስተር ዩኒቨርስቲ "ኢስትማን የሙዚቃ ት/ቤት በ1954 ዓ.ም በመጀመሪያ ዲግሪ ከተመረቁ በኃላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የያሬድ ሙዚቃ ት/ቤትን መሠረቱ።

የት/ቤትም የመጀመሪያው ዳይሬክተር ከመሆናቸውም ባሻገር በአዲስ አበባ የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር (ወ.ወ.ክ.ማ) በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የበጎ አድራጎት ድርጅት የዓይነ ስውራን ት/ቤት እና በመሳሰሉ የወጣቶች ማኅበራት እየተገኙ የሙዚቃ ትምህርት ይሰጡ ነበር።

የያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት ዳይሬክተር ሆነው ከ1955 እስከ 1958 ዓ.ም ድረስ ባገለገሉበት ወቅት በንጉሠ ነገሥቱ "ብሔራዊ የሙዚቃ አቀናባሪ" ተብለው ከመሠየማቸው ሌላ ለባህላዊ ጉዳዮች ላደረጉት የላቀ አስተዋፅዖም በ1954 ዓ.ም  የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በጎ አድራጎት ድርጅት ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የ75ተኛ የልደት በዓል በተከበረበት በዚሁ ዓ.ም በሀንጋሪ መንግሥት ተጋብዘው ወደ ቡዳፔስት በመጓዝ ታዋቂውን  "እረኛው ባለዋሽንት" እና "ኢትዮጵያ ሲንፎረያ" የተባሉትን ሁለት ድርሰቶቻቸውን በአቀናባሪነት በኦርኬስትራ መሪነት አቅርበዋል፤ በሸክላም  አሳትመዋል።

በብዙዎች አዕምሮ ውስጥ የማይጠፋውን "እረኛው ባለዋሽንት" የሚል መጠርያ የሰጡትን  ረቂቅ  ሙዚቃ  ደርሰው፣ በሀንጋሪ ፊሊሀርሞኒ ኦኬስትራ ለህዝብ ለማስደመጥ  ወደ አዳራሽ ባቀኑበት ወቅት ሀንጋሪያውያን በጥቁሩ የረቂቅ ሙዚቃ  አዘጋጅና  ኮንዳክተር ላይ  ሊስቁ ወደ አዳራሹ ተመሙ። እንስቃለን እንሳለቃለን ብለው ወደ አዳራሹ የገቡት ሃንጋሪያውያኑ  በፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ  ሥራ ተደንቀዉ  እጃቸውን በአፋቸው ጭነው  በሀገራቸው በጊዜው  ታዋቂ በነበረው  ሙዚቀኛ ኮዳይ  ስም ይጠሩትና  ያደንቁት ተያያዙ።

“ጥቁሩ ኮዳይም" በሀንጋሪ የፕሮፌሰሩ መጠርያ ሆነ። ለወትሮው በመሣርያ የተቀነባበረ በረቂቅ ሙዚቃ በአውሮፓውያን ዘንድ ብቻ ተወዳጅ  ሆኖ ይሳል ነበርና ፕሮፌሰር አሸናፊ ይህንን አመለካከት በብቃታቸው መስበር ችለዋል።

"እረኛው ባለዋሽንት" ሥራ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለጥሞና የሚደመጥ፣ የፕሮግራም ማጀቢያ በመሆን አየር ላይ በመዋል  ለዘመናት ተወዳጅነትን  ያተረፈ ረቂቅ ሙዚቃ ለመሆን በቃ።

ብዙዎች "እረኛው ባለዋሸንት" የተሰኘው ሙዚቃ በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንደዚህ እንዲወደድ ያደረገው  ፕሮፌሰር አሸናፊ  በሀገረኛ ለዛ ስላዘጋጁት ነው  ብለው ያምናሉ። እውነትም እኝህ  የሙዚቃ ሊቅ  ለሀገርኛ የሙዚቃ እድገት  ትልቅ አሰሰተዋፅኦ ያበረከቱ ናቸው ።

 ከእረኛው ባለዋሽንት በተጨማሪም፦

  1. የኢትዮጵያ ሰላም፣
  2. የፍቅር አንሰር፣
  3. የእሳት እራት፣
  4. የተማሪ ፍቅር፣
  5. የሀገራችን ህይወት፣
  6. ኒርቫኒክ ፋንታሲ፣

የተሰኙ ረቂቅ ሙዚቃዎችን  ለአድማጭ ጆሮ  ያደረሱ የሙዚቃ ደራሲ አቀናባሪ እና ኮንዳክተር ናቸው።

እናታቸው በሚጫወቱት በገና ተማርከው ወደ ሙዚቃው ዓለም እንደገቡ የሚነገርላቸው ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ፤  ሙዚቃን ከሰው ልጅ አኗኗር  ጋር በሚያጠናው  ኢትኖ ሚውዚኮሎጂ ዘርፍ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ሠርተዋል።

እ.ኤ.አ ከ1970ዎቹ ጀምሮ በረዳት ፕሮፌሰርነት የኢትኖሚውዚኮሎጂ ፕሮግራም ዳሬክተር በመሆን በኒውዮርክ  ዩኒቨርስቲ ክዊንስ ኮሌጅ  እና በማሳቹሴትስ ብራንዲስ ዩኒቨርስቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ለ19 ዓመታት በፍሎሪዳ ዩኒቨርስቲ መጀመሪያ በፕሮፌሰርነት እና በኋላም የዩኒቨርስቲው "የጥቁር አሜሪካውያን የባህል ማዕከል" ዳሬክቶር በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

የሙዚቃ ደራሲ እና አቀናባሪው ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ የተለያዩ መጻሕፍትንም ለአንባቢያን አድርሰዋል። ከነዚህም መካከል፡-

  1. የሙዚቃ ሰዋሰው መማርያ መጽሐፍ በአማርኛ፣
  2. ኮንፌንሽን ልቦለድ፣ እና
  3. root of black music የተሰኙ መፅሀፍት ተጠቃሽ ናቸው።

የሙዚቃ ሊቁ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ በ1990 ዓ.ም በ60 ዓመታቸው ህይወታቸው አልፏል።

እኝህ የሙዚቃ ሊቅ በማቋቋም እረገድ ትልቁን ሚና በተጫወቱበት እና የመጀመሪያ ዳይሬክተር ሆነው ባገለገሉበት  ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት  በስማቸው የተሰየመው "ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ  የፐርፎርሚንግ አርት ማዕከል" በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።

የአንጋፋው የሙዚቃ ትምህርት ቤት የመጀመርያው ዳሬክተር እና የሙዚቃ ሊቅ የነበሩት ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ውስጥ  ትልቅ አሻራ ያሳረፉ  እና ዘመን አይሽሬ  ሥራዎችን ያበረከቱ ሊቅ ነበሩ።

በናርዶስ አዳነ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top