የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በሀገር ግንባታ ላይ ጉልህ ድርሻ አላቸው - የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጌትነት ታደሰ

7 Days Ago
የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በሀገር ግንባታ ላይ ጉልህ ድርሻ አላቸው - የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጌትነት ታደሰ

የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በሀገር ግንባታ ላይ ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከአፋን ኦሮሞ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ጋር ተወያይቷል፡፡

በ”ኢቢሲ ለጥበብ” የውይይት መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ የኢቢሲ የአፋን ኦሮሞ ቻናል የይዘት ማሻሻያ በማድረግ እና አዳዲስ ፎርማቶችን በመጨመር በቅርቡ እንደሚመረቅ አስታውቀዋል፡፡

“ኢቢሲ የጥበብ፣ የዕውቀት እና የመረጃ ቤት ነው” ያሉት አቶ ጌትነት ታደሰ፤ ቻናሉ ለኦሮምኛ ቋንቋ እና ባህል እድገት የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ኮርፖሬሽኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የሚዲያ ኮምፕሌክስ መገንባቱን በማስታወስ፤ የተቋሙን ስም የሚመጥን የይዘት ማሻሻያ በማድረግ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኢቢሲ ለይዘት የሚሆን ተዝቆ የማያልቅ የዘመናት ሐብት እንዳለው ያወሱት አቶ ጌትነት ታደሰ፣ በአፋን ኦሮሞ የሚሰሩ አርቲስቶችም ይህን ሐብት በሙያቸው ወደ ጥበብ ቀይረው ለህዝቡ በማድረስ ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ለፈጠራ የሚመች ሁኔታ መፈጠሩን በመግለጽም “ኑ በጥበብ ሀገር እንገንባ” ሲሉ ለአፋን ኦሮሞ የጥበብ ባለሙያዎች ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊ የአፋን ኦሮሞ የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎችም፤ ከኮርፖሬሽኑ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ 

ኮርፖሬሽኑ በአፋን ኦሮሞ የ24 ሰዓት ስርጭት መጀመሩ ለኦሮሞ ህዝብ ጥበብ እድገት የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አመላክተዋል፡፡

ኢቢሲ ለብዝሃነት ትኩረት በመስጠት በባህር ዳር፣ በመቐለ፣ በሀረሪ፣ በሀዋሳ እና በመቱ ቅርጫፎችን ከፍቶ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን በቅርቡም በሶዶ እና በጋምቤላ የክልል ቅርንጫፍ ለመክፈት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top