በፈረንጆቹ 2030 ኢትዮጵያ 22 ሚሊዮን ሄክታር የተጎዳ መሬት ለማከም ቃል በገባቸው መሰረት በቁርጠኝነት እየሰራች ነው - የኢትዮጵያ ደን ልማት

2 Days Ago
በፈረንጆቹ 2030 ኢትዮጵያ 22 ሚሊዮን ሄክታር የተጎዳ መሬት ለማከም ቃል በገባቸው መሰረት በቁርጠኝነት እየሰራች ነው - የኢትዮጵያ ደን ልማት

ኢትዮጵያ በቦን ቻሌንጅ ውል ስምምነት እና በኒውዮርክ ዲክላሬሽን መድረክ በፈረንጆቹ 2030 22 ሚሊዮን ሄክታር የተጎዳ መሬት ለማከም ቃል በገባችው መሰረት በአለም አቀፍ ደረጃ በአረንጓዴ ኢኮኖሚያ ያላትን አስተዋፅኦ እያሳደገች እና በቁርጠኝነት እየሰራች እንደምትገኝ የኢትዮጵያ ደን ልማት ገለፀ፡፡  

ለዚህም የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብሩ ሃገሪቱ ለአየር ንብረት ለውጥ ምን እየሰራች እንደሆነ የምተሳይበት መሆኑን በኢትዮጵያ ደን ልማት የአረንጓዴ አሻራና ሰው ሰራሽ ደን መሪ ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አበሩ ጠና በተለይ ለኢቢሲ ሳይበር ገልፀዋል፡፡

መርኃ ግብሩ የማህበረሰቡን ተነሳሽነት ከማሳደግ ባሻገር የሀገራችንን ገፅታ የምንገነባበት ነውም ብለዋል፡፡

ይህን መሰል ሃሳቦች ከዚህ ቀደም የነበሩ ቢሆንም መንግስት በወሰደው ቁርጠኝነት አሁን ያለው ውጤት ሊመዘገብ መቻሉን ያነሳሉ፡፡

በቦን ቻሌንጅ እና በኒውዮርክ ዲክላሬሽን መድረክ ሀገራችን በፈረንጆቹ 2030 22 ሚሊዮን ሄክታር የተጎዳ መሬት አክማለሁ በማለት ቃል መግባቷን ያስታወሱት አስፈፃሚው፤ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብሩ የዛ ማሳያ አንዱ አካል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡  

በዚህም ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በተሰሩ ስራዎች ከፍተኛ ለውጥ ማስመዝገብ መቻሉንም ነው ያነሱት፡፡

አያይዘውም የጉረቤት ሀገራት ይህንን ፈለግ እየተከተሉ መሆኑንና ለዚህም ኬንያ ተጠቃሽ ሀገር መሆኗን አንስተዋል፡፡

ሀገራችን ለዓለም የአየር መበከል ያላት አስተዋፅኦ ውስን ቢሆንም እየሰራቻቸው ያሉ ስራዎች ግን ከፍተኛ ነው ሲሉም ይገልፃሉ፡፡

አክለውም ኢትዮጵያ አካባቢን መልሶ በማልማት፣ በአረንጓዴ ኢኮኖሚያ ያላትን አስተዋፅኦ በማሳደግ፣ የተጎዱ መሬቶችን በመመለስ እና በማከም እየሰራችው ያለው ስራ ከዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ጋር የሚያቀራርብ ነው ይላሉ፡፡

ይህም በተለይ ለአየር መበከል ከፍተኛ ድርሻን የሚይዙ ሀገራት ያለባቸውን የካሳ ክፍያ ኃላፊነት እንዲወጡ ያስችላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top