ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ የአማራ ክልል የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን አስጀመሩ

3 Days Ago
ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ የአማራ ክልል የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን አስጀመሩ
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ የክልሉን የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዛሬ በኮምቦልቻ ከተማ አስጀምረዋል።
 
በመርሐ-ግብሩ ማስጀመሪያ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች የአመራር አባላት ተገኝተዋል።
 
በዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት፤ በክረምት በጎ ፈቃድ ችግኝ በመትከል፣ደካሞችን በመርዳት፣ማዕድ በማጋራት፣ አካባቢን በማፅዳት ለሁለተናዊ እድገት መስራት ያስፈልጋል።
"በመረዳዳት ፣ በመተጋዝ ህብረተሰቡን ማገልገልም ይገባል" ብለዋል።
 
የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ እርዚቅ ኢሳ እንደገለጹት፤ በየዓመቱ በሚሰሩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ህብረተሰቡን በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
 
በዘንድሮው ክረምትም ከ8 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰማሩ ፈቃደኞች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
 
በዚህም የአቅመ ደካሞችን ቤት አዲስ መስራትና መጠገን፣ ደም መለገስ፣ ችግኝ መትከል፣ ጽዳትና ውበት ፣ አርሶ አደሮችን በማገዝና በሌሎችም እንደሚከናወን ጠቁመዋል።
 
በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም ወጣቶች፣ ባለሃብቶችና ሌሎችም ህብረተሰቡን በገንዘብ፣ በጉልበትና በቁሳቁስ ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት አስተዋጽኦ በማበርከት የመንግስትን የልማት ክፍተት ለመሙላት ያግዛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
 
አገልግሎቱ "ሰላም ለሁሉም፣ ለሁሉም ሰላም" በሚል ሩጫ፣ በአቅመ ደካሞች ቤት ስራ፣ ደም ልገሳ፣ ማዕድ በማጋራትና በችግኝ ተከላ ዛሬ ተጀምሯል።
 
በመርሃ ግብሩ ላይ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ የክልል፣ ዞንና የከተማ አመራር አባላት፣ በጎ ፈቃደኞችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top