አቶ ጌታቸው ረዳ በትግራይ ክልል የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብርን አስጀመሩ

4 Days Ago
አቶ ጌታቸው ረዳ በትግራይ ክልል የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብርን አስጀመሩ

የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርን በዛሬው ዕለት አስጀምረዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብሩን በክልል ደረጃ ዛሬ በይፋ ያስጀመሩት በትግራይ ደቡባዊ ዞን ውስጥ ነው።

በመርሀ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ አቶ ጌታቸው ረዳ እንደተናገሩት፤ በክልሉ የተራቆቱ ተራሮች መልሰው እንዲያገግሙ ሁሉም ህብረተሰብ በችግኝ ተከላ መርሀ ግብር በንቃት ተሳታፊ መሆን ይጠበቅበታል።

ባለፉት ዓመታት የወደሙ ደኖችን ለመመለስና አረንጓዴ አካባቢን ለመፍጠር ችግኝ መትከልና መንከባከብ ወሳኝ ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል።

የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዓለምብርሃን ሀሪፈዮ በበኩላቸው፤ በዚህ ዓመት በ144 የችግኝ ማዕከላት ችግኞች የማፍላት ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩም 38 ሺህ ሄክታር መሬት የማዳን ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ የተከላቸውን ችግኞች በመንከባከብ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ እውን እንዲሆን ማድረግ አለበት ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top