በመካከለኛው አዋሽ የቅድመ ጎርፍ መከላከል ስራ በይፋ ተጀመረ

2 Days Ago
በመካከለኛው አዋሽ የቅድመ ጎርፍ መከላከል ስራ በይፋ ተጀመረ

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በመካከለኛው አዋሽ የቅድመ ጎርፍ መከላከል ስራዎችን በይፋ አስጀመረ።

የጎርፍ ቅድመ መከላከል ስራውን በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የሚኒስትሩ አማካሪ ሞቱማ መቃሳና ሌሎች አመራሮች በአፋር ክልል ገዋኔ ወረዳ ተገኝተው አስጀምረዋል።

ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በመካከለኛው አዋሽ የጎርፍ ቅድመ መከላከል ስራ የሚከናወነው በገዋኔ፣ ገላእሎ፣ ዱለሳ እና አሩካ ወረዳዎች መሆናቸውም ተጠቁሟል።

በመካከለኛው አዋሽ አራቱ ወረዳዎች የሚከናወነውን የቅድመ ጎርፍ የመከላከል ስራዎቹን አቅሌሲያ እና ሀቢብ ሁሴን የግንባታና ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን የተሰኙ ድርጅቶች ያከናውናሉ ተብሏል።

የቅድመ ጎርፍ መከላከል ስራዎቹ በሁለት ወራት ውስጥ የሚጠናቀቁ ሲሆን፤ በጎርፍ ምክንያት በክረምት ወራት ከአካባቢያቸው ለሚፈናቀሉ ነዋሪዎች እፎይታን እንደሚሰጥ ይጠበቃል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር አማካሪ ሞቱማ መቃሳ እንደገለጹት፤ የቅድመ ጎርፍ መከላከል ስራዎቹ በአጭር ጊዜ ለማህበረሰቡ መፍትሄ ለመስጠት የሚከናወን ነው።

ኮንትራክተሮች በተቀመጠው ጊዜ ስራውን በማከናወን ያለባቸውን ማህበራዊ ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡም ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከ515 ሚሊየን ብር በላይ በሚሆን ወጪ በላይኛው፣ መካከለኛው እና የታችኛው አዋሽ ተፋሰስ ወረዳዎች የቅድመ ጎርፍ መከላከል የሲቪል ስራዎችን ለማከናወን ከአምስት ተቋራጭ ድርጅቶች ጋር ሰሞኑን የውል ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top