ኢትዮጵያ እና አዘርባጃን በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ በትብብር ለመስራት ተወያዩ

2 Days Ago
ኢትዮጵያ እና አዘርባጃን በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ በትብብር ለመስራት ተወያዩ
ኢትዮጵያ እና አዘርባጃን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመከላከል በትብብር ለመስራት ተወያይተዋል።
 
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ የአዘርባጃንን ልዑካን ቡድን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
 
በዚህ ወቅት ሁለቱ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርሱ ጉዳቶችን በዘላቂነት ለመከላከል ተቀራርበው መሰራት በሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
 
አፈ-ጉባዔ ታገሰ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ቀዳሚ አጀንዳ አድርጋ እየሰራች እንደሆነ ገለጸው፤ ለዚህ ማሳያም በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ በርካታ ተግባራት ተከናውኖ ተጨባጭ ውጤት መታየቱን አስገንዝበዋል።
 
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶ/ር ፍጹም አሰፋ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ዘርፍ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች በመሆኑ በርካታ ለውጦች አየታዩ መሆኑን ጠቅሰዋል።
 
ቀጣይነት ያለው ውጤት ለማስመዝገብም የኢትዮጵያ እና የአዘርባጃን ትብብር መጠናከር አስፈላጊ ነው ብለዋል ሚኒስትሯ።
 
በአዘርባጃን የኢኮሎጂ እና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ሚኒስትር ሙክህታር ባባየቭ በበኩላቸው፤ ሀገራቸው በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ፈቃደኛ መሆኗን ገልጸዋል።
 
አዘርባጃን በአየር ንብረት ለውጥ በሚከሰቱ እንደ ድርቅ፣ጎርፍ እና ተያያዥ አደጋዎችን በቅድመ መከላከል ረገድ ያላትን የካበተ ልምድ ለኢትዮጵያ ማካፈል እንደምትችልም ሚንስትሩ አክለዋል።
 
አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ እና የአዘርባጃን ልዑካን ቡድን በምክር ቤቱ ግቢ ውስጥ ችግኝ በመትከል አሻራቸውን ማስቀመጣቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top