ኢትዮጵያ የባህር በር የመፈለጓ መሰረታዊ መነሻ የህልውና ጉዳይ ነው - የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ

2 Mons Ago
ኢትዮጵያ የባህር በር የመፈለጓ መሰረታዊ መነሻ የህልውና ጉዳይ ነው - የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ

የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ ለቀጣናው ሀገራት በሰላማዊ መርህ የቀረበ ህልውናን እና ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ጉዳይ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች ገለጹ።

የኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ፈትሂ ማሕዲ፤ ኢትዮጵያ በከፍኛ ፍጥነት እያደገ ያለ ኢኮኖሚና የህዝብ ቁጥር ያላት በመሆኗ አማራጭ ወደብ የግድ ያስፈልጋታል ብለዋል።

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ማደግ፣ የወጪና ገቢ ንግድ መጨመርን ተከትሎ አንድ ወደብ ብቻ ኢኮኖሚዋን ሊሸከም እንደማይችል ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በር የመፈለጓ መሰረታዊ መነሻ የህልውና ጉዳይ ነው ያሉት ምክትል ሰብሳቢው ከሶማሌላንድ ጋር ከተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ባሻገር ሌሎች ጥረቶችም ይቀጥላሉ ብለዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘቷ የግድ ቢሆንም የምትከተለው መርህ ሰላማዊ አማራጭ መሆኑን በመንግስት ደረጃ መገለጹንም ነው ዶክተር ፈትሂ የተናገሩት።

የባህር በር ጥያቄው ዋነኛ ግብ ኢትዮጵያና ጎረቤት ሀገራት ህልውናቸውን በትስስር የሚያረጋግጡበትን የነገ የአብሮነት ጉዞ የተለመ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አንድም ጊዜ ሌላ ሀገርን በኃይል ወርራ ወደብ ለማግኘት ያደረገችው ጥረት የለም ያሉት ዶክተር ፈትሂ አቋሟ ሰላማዊ አማራጭ ብቻ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ዶክተር ባለው ባዬ በበኩላቸው አሁን በሀገሪቱ ያለው የህዝብ ቁጥር፣ ቀጣናዊ ተለዋዋጭ ሁኔታና የኢኮኖሚ እድገት ያለ ወደብ ብዙ እርምጃ አያስኬድም ብለዋል።

መንግስት አጀንዳውን ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ጉዳይ አድርጎ እንደያዘውና የወደብ አማራጮችን ለማስፋት እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል።

በቅርቡ ከሶማሌላንድ ጋር የተደረሰው የመግባቢያ ስምምነትም የሰጥቶ መቀበል መርህን የተከተለ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ በህዝብ ቁጥርም በኢኮኖሚ እድገትም ቀዳሚ መሆኗን ገልጸው ከዚህ አኳያ እያደገ የመጣውን ፍላጎት በብቃት የሚሸከም ወደብ እንደሚያስፈልጋት ተናግረዋል።

የኮሚቴው አመራሮች ቀይ ባህር የዓለም ንግድ ዋነኛ መተላለፊያ፣ የኃያላን የትኩረት ነጥብ መሆኑን ገልጸው ኢትዮጵያ ካላት ቅርበት አንጻር ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ በዝምታ አትቀመጥም ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከወጪ ንግዷ ባሻገር ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ አንገብጋቢ የሆኑ እንደ መድሃኒት፣ ማዳበሪያ፣ ነዳጅና መሰል ምርቶችም የሚጓጓዙት በዚሁ መስመር በመሆኑ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ያሳስቧታል ነው ያሉት።

ቀጣናው ከዘጠኝ ያላነሱ ሀገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር ብዙ ሺህ ማይል ተጉዘው የጦር ሰፈር ሰርተው የሚንቀሳቀሱበት የመሆኑን ያህል፣ አሸባሪዎች፣ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎችና ህገወጥ የጦር መሳሪያ ንግድ የሚዘወተርበት መሆኑ ለኢትዮጵያ ስጋት ነው ብለዋል።

በመሆኑም ኢኮኖሚያዊ ህልውናዋን እና ሉዓላዊ ደህንነቷን ለማስከበር የባህር ኃይሏ የሚንቀሳቀስበት የባሀር በር እንዲሁም ለንግድ አማራጭ ወደብ የግድ እንደሚያስፈልጋት ተናግረዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top