ሕዝቡ በፍትህ ሥርዓቱ ላይ እምነት እንዲኖረው በጥራት መሥራት እንደሚገባ ተጠቆመ

9 Mons Ago 861
ሕዝቡ በፍትህ ሥርዓቱ ላይ እምነት እንዲኖረው በጥራት መሥራት እንደሚገባ ተጠቆመ

ሕዝቡ በፍትህ ሥራዓቱ ላይ እምነት አንዲኖረውና ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ በፍትህ ጥራት ላይ መሥራት እንደሚገባ ተጠቁሟል።

በሀረሪ ክልል ሀረር ከተማ ሲካሄድ የነበረው የሀገር አቀፍ የህግ አውጪዎች የምክክር መድረክ ተጠናቋል።

በመድረኩ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት፣ የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) እንዲሁም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ እፀገነት መንግሥቱ የፍርድ ቤቶች እና የፍትህ ተቋማት ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈፃፀምና የሱፐርቪዥን ሪፖርት አቅርበዋል።

በቀረበው የአፈፃፀም ሪፖርት ላይም በተሣታፊዎች ሰፊ ውይይት ተደርጓል።

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በውይይቱ ማጠቃለያ በሰጡት አስተያየት፥ ኅብረተሰቡ በፍትህ ሥርዓቱ ላይ እሮሮ እያሰማ ስለሆነ በፍትህ ሥርዓቱ ላይ የሚነሳውን የጥራት ችግር ለመቅረፍ ሕጋዊ አሠራርን የሚከተሉ የፍትህ ተቋማትን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።

አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ አክለውም ኀብረተሰቡ የፍትህ ተቋማት በሚሰጡት አገልግሎት እምነት ኖሮት ወደ ፍትህ ተቋማት እንዲመጣ ለማድረግ የፍህት ተቋማቱ በቴክኖሎጂ ተደግፈው ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚጠበቅባቸው መሆኑን አመላክተዋል።

የፍትህ ሥርዓቱን ማዘመን ለአገሪቱ ሰላምና ፀጥታ ወሳኝ በመሆኑ ኅብረተሰቡ በፍትህ ሥርዓቱ ላይ የሚነሳውን እሮሮ ለማስቀረት ከወረዳ እስከ ፌዴራል ያሉ የፍትህ አካላት በቅንጅት ሠርተው ዘላቂ መፍትሔ ማስቀመጥ እንዳለባቸው አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ጨምረው አሳስበዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር በሰጡት አስተያየት፥ የፍትህ ሥርዓቱን ለማዘመን እየተሠራ ያለው ትራንስፎርሜሽን ወደ ኋላ እንዳይመለስና ውጤታማ እንዲሆን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እያደረገው ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ሎሚ በዶ፥ በፍትህ አካላት ላይ የሚነሳው እሮሮ የፍትህ ችግር ብቻ ሳይሆን የመልካም አስተዳደር፣ የሰላምና ፀጥታ ችግር በመሆን ሕዝብና መንግሥትን እያራራቀ ስለሆነ የፍትህ ጥራትን ለማስጠበቅ ከወረዳ እስከ ፌዴራል በሚሠራው ትራንስፎርሜሽን ዘላቂ መፍትሔ ማስቀመጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የአንድ ተቋም መጠናከር ብቻ የፍትህ ሥርዓቱን ሊያሻሽለው ስለማይችል ከወረዳ እስከ ፌዴራል ያሉ የፍትህ አካላት ተቀናጅተው በመሥራት የተጀመረውን ትራንስፎርሜሽን ማስቀጠል እንዳለባቸው ወ/ሮ ሎሚ በዶ ጨምረው አሳስበዋል።

የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት፥ ኅብረተሰቡ በፍትህ ሥርዓቱ እምነት እንዲኖረው በየደረጃው ባሉ የፍትህ አካላት የትራንስፎርሜሽን ሥራዎችን ለማስቀጠል ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፤ የክልል አመራሮች እየተባበሩ ባለመሆናቸው ከወረዳ እስከ ክልል ያሉ አመራሮች ትብብር እንዲያደርጉ የክልል አፈ ጉባኤዎችን ጠይቀዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት፥ በዳኝነት በኩል ያለውን የሕዝብ እሮሮ ለማስቀረት የዳኝነት ነፃነትን በማይነካ መልኩ የፍትህ ጥራትን ለማሻሻል በትብብር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በምክር ቤቱ የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እፀገነት መንግሥቱ፥ በኅብረተሰቡ ዘንድ በተፈጠረው ንቃተ ሕግ ኅብረተሰቡ መብቱን ለማስጠበቅ እስከ ፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት፤ የሕግ ስህተት አለ ብሎ ሲያስብም እስከ ሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባኤና ፌዴሬሽን ምክር ቤት በመምጣት እየተከራከረ መብቱን ለማስጠበቅ ልምምድ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።

በየደረጃው ያሉ የፍትህ አካላት የፍትህ ጥራትን ለማስጠበቅ ጥሩ ተሞክሮ ካላቸው የፍትህ አካላት ተሞክሮ መውሳድ እንደሚገባቸውም ወ/ሮ እፀገነት ማሳሰባቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top