የተረጋጋ የፋይናንስ ስርዓት እንዲፈጠር የሚረዱ ስራዎች መጠናከር እንዳለባቸው ተገለጸ

9 Mons Ago 934
የተረጋጋ የፋይናንስ ስርዓት እንዲፈጠር የሚረዱ ስራዎች መጠናከር እንዳለባቸው ተገለጸ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተረጋጋ የፋይናንስ ስርዓት እንዲፈጠር ለማስቻል የሚረዱ ፈርጀ ብዙ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው በብሔራዊ ባንክ ተገኝቶ ከባንኩ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር ተወያይቷል።

በውይይቱም፥ ባንኩ የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር፣ የውጭ ምንዛሪ አማራጭ ዘርፎችን በማብዛት እንዲሁም ጤናማና የተረጋጋ የፋይናንስ ሥርዓት በመዘርጋት የፋይናንስ አካታችነትን ለማሳደግ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት ተገልጿል።

በተጨማሪም ዲጂታላይዜሽንና የቴክኖሎጂ አቅምን ከማጎልበት፣ በክህሎት የዳበረ የሰው ሀብት ከማፍራት እንዲሁም መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አኳያ ባንኩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባውም ተመላክቷል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ፥ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከምንጊዜውም በበለጠ ሀገር በቀል የሆኑ የግልና የመንግሥት ባንኮች በብዛት በባንክ ኢንዱስትሪው ተሰማርተው ይገኛሉ ብለዋል።

ባንኮቹ ገበያው ላይ የሚያደርጉት ውድድር ጤናማ እንዲሁም ሕብረተሰቡን እና ሀገርን የሚጠቀም ሆኖ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል።

የብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ በበኩላቸው፥ የገበያ ዋጋ ንረትን ማርገብ ከባንኩ ቁልፍ ተግባራት ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ባንኩ በቅርቡ የወሰዳቸው የገንዘብ ፖሊሲ እርምጃዎች የዋጋ ንረትን በማርገብ፣ የባንክ ብድር ዕድገትን በመግታትና የመንግሥትን የቀጥታ ብድር መጠን በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ አዎንታዊ ውጤት እያስገኙ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ከፋይናንስ ጤናማነት መለኪያዎች አንጻር ሲገመገም የፋይናንስ ዘርፉ ጤናማ፣ ትርፋማ እና የተረጋጋ እንደሆነ የባንኩ ገዢ ማስረዳታቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top