ኢትዮጵያ ዘለቄታ ያለው አማራጭ የአውሮፕላን ነዳጅ ለማምረት የሚያስችላትን ድጋፍ ከፈረንሳይ መንግሥት አገኘች

8 Mons Ago
ኢትዮጵያ ዘለቄታ ያለው አማራጭ የአውሮፕላን ነዳጅ ለማምረት የሚያስችላትን ድጋፍ ከፈረንሳይ መንግሥት አገኘች

ዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) የአቪዬሽን አካባቢ ጥበቃን እንደ አንድ ስትራቴጂክ ዓላማ አድርጎ እየሰራበት ይገኛል።

ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ የአቪዬሽን አከባቢ ጥበቃ በተለይም የካርበን ልቀት ቅነሳ ጉዳይ በድርጅቱ አባል አገራት ዘንድ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በድርጅቱ ውስጥ ዋነኛ መነጋገሪያና አከራካሪ አጀንዳ ሆኗል።

ዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት እ.ኤ.አ በ2050 የአቪዬሽን በካይ ጋዞችን በተለይም የካርቦን ዳይ ኦክሳይድ (CO2) ልቀትን የተጣራ ዜሮ ላይ ለማድረስ ራዕይ ይዞ በትልቅ ትኩረት እየሰራበት ካለው የረጅም ጊዜ የበካይ ጋዞች ልቀት ቅነሳ ግብ ፕሮግራሞች መካከል ዘላቂነት ያለው የአቪዬሽን ነዳጅን ማምረትና መጠቀም አንዱና ዋነኛው ነው።

በአሁኑ ጊዜ ለአውሮፕላን እየዋለ ያለው ነዳጅ የበካይ ጋዞችን በብዛት ወደ አየር የሚለቅ ስለሆነ እና በከባቢ አየር ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ስለሚያሳድር ዝቅተኛ የበካይ ጋዞች ልቀት ያለው አማራጭ የአቪዬሽን ነዳጅ እንዲመረትና በስራ ላይ እንዲውል በዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት በኩል አቅጣጫ ተቀምጧል።

በዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ዕቅድ መሰረት እ.ኤ.አ. በ2050 የአቪዬሽን እንቅስቃሴዎች ከመደበኛው ነዳጅ ወደ ተፈጥሮ ተኮር ነዳጅ በዘላቂነት የተሸጋገሩ እንዲሆኑ እና የአቪዬሽን በካይ ጋዞችን ልቀት እ.ኤ.አ በ2050 የተጣራ ዜሮ ላይ ለማድረስ እየተሰራ ይገኛል።

ለዚህ ዕቅድ አዎንታዊነት ልዩ ትኩረት የተሰጠው ደግሞ ከተፈጥሮ ዕፅዋትና ሌሎች ግብዓቶች ሊለማ የታቀደው እና እስከ 80 በመቶ የካርቦን ልቀትን እንደሚቀንስ የታመነበት ዘላቂነት ያለው የአቪዬሽን ነዳጅ ነው።

ዘላቂነት ያለው የአቪዬሽን ነዳጅ በቴክኖሎጂ በመታገዝ እና የተለያዩ ዕጽዋቶችን፣ ደረቅ ተረፈ ምርቶችን እና ከፋብሪካ የሚወጣውን ካርቦን በመጠቀም የሚመረት የአውሮፕላን ነዳጅ ነው።

ይህን መሰረት አድርጎ እ.ኤ.አ ከህዳር 20-24/2023 በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ዱባይ እየተካሄደ ባለው 3ኛው የአቪዬሽን እና አማራጭ ነዳጅ ኮንፍረንስ ላይ ዘላቂነት ያለው የአቪዬሽን ነዳጅ ምርትና አጠቃቀም ዙሪያ ዓለም አቀፍ ማዕቀፎች፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የአቅም ግንባታ እና የፋይናንስ አጀንዳዎች ላይ ጥናታዊ ፅሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ኢትዮጵያም በኮንፍረንሱ በተነሱ ወሳኝ በሆኑ ርዕሶች ላይ በንግግር እና በጽሑፍ አስፈላጊውን ተሳትፎ እያደረገች ትገኛለች።

ከዚሁ ኮንፍረንስ ጎን ለጎንም ከፈረንሳይ መንግሥት ጋር ቀደም ሲል በተካሄደው የሁለትዮሽ ውይይት መሰረት በኢትዮጵያ ዘላቂነት ያለው የአቪዬሽን ነዳጅ ልማትን የተመለከቱ ጥናቶችን ለማድረግ የሚረዳ የፋይናንስ ድጋፍ ይፋ ተደርጓል።

ይህ በፈረንሣይ የገንዘብ ድጋፍ የሚካሄደው አዲስ ፕሮጀክት ዘላቂ የአቪዬሽን ነዳጅ ፕሮጀክቶችን ኢኮኖሚያዊ ምዘናዎችን፣ የቢዝነስ እቅድ ትግበራን እና የመንግሥትና የግል ሴክተር የፋይናንስ ዕድሎችን የመለየት ሥራን ይሸፍናል።

ድጋፉ ይፋ በሆነበት ስነ ስርዓት ላይ የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ዋና ጸሐፊ፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደንጌ ቦሩ እና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሰልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግሥቴ ተገኝተዋል።

አቶ ደንጌ ቦሩ በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃን በተመለከተ ያላትን ቁርጠኝነትና በዘርፉ በተጨባጭ እየተከናወኑ ያሉት ተግባራትን አብራርተዋል።

በተጨማሪም፥ በፈረንሳይ መንግሥት በኩል የተሰጠው ድጋፍ ዘለቄታ ያለው አማራጭ የአውሮፕላን ነዳጅን ለማምረት ኢትዮጵያ ያላትን ዕቅድ በማሳካት ረገድ የሚኖረውን ከፍተኛ አስተዋጻኦ በመግለጽ የፈረንሳይን መንግሥት ማመስገናቸውን ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top