ባለፉት 3 ወራት ዲኘሎማሲውን ወደ ከፍታ መመለስ ያስቻሉ ስራዎች መሰራታቸው ተገለፀ

11 Mons Ago 1361
ባለፉት 3 ወራት ዲኘሎማሲውን ወደ ከፍታ መመለስ ያስቻሉ ስራዎች መሰራታቸው ተገለፀ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2016 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የስራ አፈፃፀም ሪፓርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዛሬው እለት ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።

በሪፖርቱ ግንኙነትን በማጠናከር፣ የኢትዮጵያን ተሰሚነት በማሳደግ እና ሚዛናዊ አቋም እንዲያዝ በማድረግ፣ የኢንቨስትመንት ፍሰትን በማሳደግና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ከውጭ በመመለስ ዲፕሎማሲው ውጤታማ እንደነበር ተነስቷል።

ባለፉት ሶስት ወራት በጎረቤት ሃገራት ከ11 በላይ ጉብኝቶችን በማድረግ ግንኙነትን የማጠናከር ስራዎች ተሰርተዋል ነው የተባለው።

በአባይ ውሃ ፍትሃዊና ምክንያታዊ አጠቃቀም እንዲኖር የሚያስችለውን ሁሉን አቀፍ የስምምነት ማዕቀፍ ቡሩንዲ እንድትፈርም ማድረግ መቻሉ ትልቅ ውጤት መሆኑ ተገልጿል።

አዲስ አጋርነትን እና ትብብርን ከመፍጠር አንፃር በሩብ ዓመቱ ከተሰሩ ስራዎች ትልቁ ስኬት ኢትዮጵያ ብሪክስን እንድትቀላቀል ማድረግ መቻሉ እንደሆነም ተነስቷል።

ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ህብረት ጋር ያለውን ግንኙነት ወደቀድሞ ለመመለስ የሚያስችሉ ሁኔታዎች መፍጠር ተችሏልም ተብሏል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በቀረበው ሪፓርት ላይ ጥያቄ እና አስተያየየት ሰንዝረው በሚኒስቴሩ የተለያዩ የስራ ሃላፊዎች ምላሽ ተሰጥቷል።

በመድረኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እንዳሉት ከኘሮጀክቶች ጋር በተያያዘ ዘግይተው የነበሩ በተለያዩ ሚሲዮኖች የሚካሄዱ የፅ/ቤት እና የአምባሳደሮች መኖሪያ ቤት ግንባታዎችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ባለፉት ሶስት ወራት የተገኙት ውጤቶች ዲኘሎማሲው ወደ ከፍታው እየተመለሰ መሆኑን የሚያሳይ ነው ያሉት ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ናቸው።

በቀይ ባህር አካባቢ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ከቀጣይ የዲኘሎማሲው ትኩረቶች አንዱ እንደሆነም አምባሳደር ምስጋኑ መጠቆማቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ዲማ ነገዎ በመዝጊያ ንግግራቸው ኢትዮጵያ አባል በሆነችባቸው ህብረቶች ውስጥ ጥቅሟን በተሟላ ሁኔታ ለማስጠበቅ ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ተቋማት ጋር በቅንጅት መሰራት አለበት ብለዋል።

በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ወደ ሃገር ቤት ከመመለስ ባሻገር በሚኖሩባቸው ሀገራት ሕጋዊ የሚሆኑበት ስራ መሰራት እንዳለበትም አሳስበዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top