በሰብዓዊ ተግባር ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን በተለያየ መንገድ ማገዝ ይገባል - አቶ ጌታቸው ረዳ

11 Mons Ago 527
በሰብዓዊ ተግባር ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን በተለያየ መንገድ ማገዝ ይገባል - አቶ ጌታቸው ረዳ

በሰብዓዊ ተግባር ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን በተለያየ መንገድ ማገዝ እንደሚገባ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ ገለጹ።

አረጋውያን፣ ሕጻናትና የአዕምሮ ሕሙማንን ለማገዝ ያለመ የአምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ዛሬ በመቐለ ከተማ ተካሂዷል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ ውድድሩን ሲያስጀምሩ፥ ለከፋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡ ወገኖችን ማገዝ ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።

በመቐለ ከተማ በሚገኘው የፍሬምናጦስ የአረጋውያን፣ የህጻናትና የአዕምሮ ሕሙማን ማገገሚያ ማዕከል ለእነዚህ ወገኖች እያደረገው ያለውን ድጋፍ በአርአያነት መከተል እንደሚገባም ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በሰብዓዊ ተግባር ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን እያገዘ መሆኑን ጠቅሰው፤ ስኬቱን ይበልጥ ለማሳደግ የሁሉም ሃላፊነት መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የፍሬምናጦስ ማገገሚያ ማዕከል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አባ ገብረመድህን በርኸ በበኩላቸው፥ ከ300 በላይ አረጋውያንና ህጻናት በማዕከሉ ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል ብለዋል።

በቀጣይ ሁለት ዓመታት ውስጥም ማዕከሉ በተሰጠው 43 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ከ2 ሺህ የሚበልጡ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ማገገሚያ ማዕከል በ3 ቢሊዮን ብር ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።

ለማዕከሉ ግንባታ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ሃላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

ዛሬ የተካሄደውን የጎዳና ላይ ሩጫ ፍሬምናጦስ ማገገሚያ ማዕከል ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጤና ቢሮ እና ስፖትር ኮሚሽን ጋር በመተባበር እንዳዘጋጁት ታውቋል።

ከሩጫ ውድድሩ የተገኘው ገቢም ለማዕከሉ ግንባታ እንደሚውል የማዕከሉ ዋና ስራ አስፈጻሚ ተናግረዋል።

በሩጫው የተሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎችም የተቸገሩ ወገኖችን ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ዛሬ በመቐለ ከተማ በተካሄደው የሩጫ ውድድር ላይ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉ ሲሆን፤ በውድድሩ ከ1ኛ እስከ 5ኛ ደረጃን ይዘው ላጠናቀቁና ለዝግጅቱ ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የማበረታቻ ሽልማቶች ተበርክተዋል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top