በእንጦጦ ፓርክ ዙሪያ የቅሚያና የውንብድና ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ ግለሰቦች በ16 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት ተቀጡ

3 Mons Ago
በእንጦጦ ፓርክ ዙሪያ የቅሚያና የውንብድና ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ ግለሰቦች በ16 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት ተቀጡ

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 በሚገኘው እንጦጦ ፓርክ ዙሪያ የቅሚያ እና የውንብድና ወንጀል ሲፈፅሙ በነበሩ ሁለት ግለሰቦች ላይ የቅጣት ውሳኔ መተላለፉን በክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የሽሮሜዳ አካባቢ ጣቢያ ፖሊስ ገለፀ።

የጣቢያው የወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ሃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ፍቅሩ ማሞ እንደተናገሩት፥ ዮናስ ዳኜ የተባለው ግለሰብ ለጊዜው ካልተያዘው ግብራበሩ ጋር በመሆን በ2015 ዓ.ም በተለያዩ ቀናት በፓርኩ ዙሪያ በሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ላይ የሃይል ተግባር በመጠቀም ጭምር የቅሚያ እና የውንብድና ወንጀል በመፈፀም ጥሬ ገንዘብን ጨምሮ የተለያዩ ንብረቶችን ሲዘርፉ ቆይተዋል።

ፖሊስ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ወንጀል ፈፃሚዎቹን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የጠቀሱት ምክትል ኢንስፔክተር ፍቅሩ ማሞ፤ ፍርድ ቤት ከቀረቡ እና የዋስትና መብት ተፈቅዶላቸው ከእስር ከተለቀቁ በኋላ በቀጠሮ ቀን ፍርድ ቤት ሳይቀረቡ መቅረታቸውን ተናግረዋል።

የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጉለሌ ምድብ ችሎት ጉዳዩን ሲመለከት ቆይቶ ሁለቱም ተከሳሾች በተደጋጋሚ ቀጠሮ ሊቀርቡ ባለመቻላቸው በሌሉበት እያንዳንዳቸው በ16 ዓመት ከስድስት ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ማስተላለፉን ምክትል ኢንስፔክተር ፍቅሩ ማሞ አስረድተዋል።

ፖሊስም ፍርደኞቹን አፈላጎ ለማረሚያ ቤት ለማስረከብ ባደረገው ጥረት ዮናስ ዳኜ የተባለው ግለሰብ ጥቅምት 18 ቀን 2016 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ሊውል መቻሉን እና ያልተያዘው ግብራበሩን ለመያዝ የክትትል ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን የምርመራ ክፍል ሃላፊው ገልፀዋል።

በእንጦጦ ፓርክ ለመዝናናት የሚመጡ ግለሰቦች ምንም አይነት የደህንነት ስጋት እንዳይሰማቸው ፖሊስ የመከላከል አቅሙን በማሳደግ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ እና ቀደም ሲል አልፎ አልፎ ይፈፀሙ የነበሩ ወንጀሎችን ማስቆም እንደተቻለ ምክትል ኢንስፔክተር ፍቅሩ ጠቅሰዋል።

ወንጀል ፈፃሚዎችን በህግ አግባብ ለማስቀጣት ጥቆማ ከመስጠት ጀምሮ ፍርድ ቤት ቀርቦ እስከ መመስከር የህብረተሰቡ ድጋፍ የበለጠ ሊጠናከር እንደሚገባም ሃላፊው መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top