በትምህርት ዘርፉ ተጨባጭ መፍትሄ ለማፈላለግ ችግሮቹ በትኩረት ሊፈተሹ ይገባል - የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

1 Yr Ago 395
በትምህርት ዘርፉ ተጨባጭ መፍትሄ ለማፈላለግ ችግሮቹ በትኩረት ሊፈተሹ ይገባል - የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

በትምህርት ስርዓቱ የሚስተዋሉ ችግሮች ሊቀረፉ እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው ይህን ያለው የትምህርት ሚኒስትርን የ2016 በጀት ዓመት እቅድ እና የሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት በገመገመበት ወቅት ነው።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የተመዘገበው ውጤት የትምህርቱ ዘርፍ ትኩረት እንደሚሻ ጠቋሚ መሆኑን ገልፀዋል።

ይህን ታሳቢ በማድረግ የ2016 በጀት ዓመት እቅድ ሊፈተሽ እንደሚገባው አሳስበዋል።

በሩብ ዓመቱ የተከናወኑ የዝግጅት ምዕራፍ ተግባራት እና ዩኒቨርሲቲዎች የመውጫ ፈተና እዲያዘጋጁ መደረጉ በጥንካሬ የሚታዩ አፈጻጸሞች መሆናቸውን የገለጹት ዶክተር ነገሪ፣ የትምህርት ውጤት ሲታይ አፈጻጸሙ ጥያቄ ውስጥ እንደሆነ ታውቆ እቅዱን እንደገና መፈተሽ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

የተማሪዎች የመማሪያ መጻህፍትን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ የትምህርት ግብዓቶች አለመሟላት የተቋሙን ልዩ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውን ዶክተር ነገሪ አስገንዝበዋል።

ለትምህርት ውድቀት ተጠያቂው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ቢሆኑም በዋናነት ትምህርት ሚኒስቴር በመሆኑ ኃላፊነት ወስዶ ሊሰራ እንደሚገባ ያሳሰቡት ዶክተር ነገሪ፤ በትምህርት ዘርፉ ተጨባጭ መፍትሄ ለማፈላለግ ችግሮቹ በትኩረት ሊፈተሹ ይገባል፣ ኩረጃ ስለቀረ ነው ብዙ ተማሪዎች የወደቁት የሚለው ፅንሰ ሀሳብ ሁሉንም አያስማም ብለዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም የተማሪዎች መማሪያ መጻህፍት የተወሰኑት ታትመው ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ ሲሆን፤ የቀሩት ደግሞ ጅቡቲ ወደብ ላይ መድረሳቸውን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናግረዋል።

የመጻህፍት ህትመት ችግሩን በዘላቂነነት ለመፍታት በአገር ውስጥ ማተሚያ እንዲቋቋም ሁለንተናዊ ጥረት እየተደረገ ነው ሲሉ መግለፃቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top