በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገር ውስጥ ባለዲግሪዎችን የስራ ቅጥር ቅቡልነት የሚያቀል የብቃት ማረጋገጫ ማዕቀፍ ሰነድ ተዘጋጀ

1 Yr Ago 965
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገር ውስጥ ባለዲግሪዎችን የስራ ቅጥር ቅቡልነት የሚያቀል የብቃት ማረጋገጫ ማዕቀፍ ሰነድ ተዘጋጀ

በትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን የስታንዳርዳይዜሽንና ብቃት ማረጋገጫ ማዕቀፍ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ታፈረ ቢጠና ለኢቢሲ እንደገለፁት፥ ማዕቀፉ ከዲግሪዎች በተጨማሪ ኢ-መደበኛና ሀገር በቀል የልምድ እውቀቶችን በሀገር ውስጥ እንዲገመገሙ በማድረግ ሌቭል እንዲሰጣቸው የሚያደርግ አሰራርንም የያዘ ሰነድ ነው።

በሰነዱ መሰረት ለትምህርት ተቋማት በተሰራጩ የተሻሻሉ ፕሮግራሞች መሰረትም ብቃት መፈተሻና የእውቅና አሰጣጥ ስርዓት ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ገቢራዊ ይደረጋል ነው ያሉት ስራ አስፈፃሚው።

በሰነድ ዝግጅት ሂደቱ ተሳታፊ የሆኑትና የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደረጄ እንግዳ በሰጡት ማብራሪያ፥ ሀገሪቱ በተለይ በምህንድስናው ዘርፍ ዓለም አቀፍ እውቅናን ለማሳደግ የዋሺንግተን አኮርድ ከተሰኘ የአሜሪካ ተቋም ጋር ለመስራት በሂደት ላይ ነች።

በሙከራ ደረጃም በዚህ ዘርፍ የጅማ፣ ባህርዳር፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በዚህ ዓለም አቀፍ ስርዓት ፕሮግራማቸውን የማስገምገም ሂደት ተጀምሯል።

እርሳቸው እንዳሉት፥ ከቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት ጀምሮ በዚሁ ስርዓት እውቅና ያላገኙ የሕክምና ዲግሪዎች በዋሺንግተን አኮርድ አባል ሀገራት በኩል ተቀባይነት አያገኙም።

ይህን ተግባራዊ ለማድረግ 'ABET' ከተሰኘ የአሜሪካ እውቅና ሰጪ ኤጀንሲ ጋር እየሰራን ነው ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።

አሁን ላይ ተዘጋጅቶ የተጠናቀቀው የብቃት ማረጋገጫ ማዕቀፍ በሚቀጥለው ዓመት ፀድቆ ስራ ላይ እንደሚውል ይጠበቃልም ብለዋል።

ማዕቀፉ ገቢራዊ ሲሆን የትምህርት መርሐ ግብሮች በስምንት ሌቭል ዓለም አቀፍ ተነፃፃሪነትን በጠበቀ መልኩ ተገምግመው እውቅና ስለሚሰጣቸው፤ ለዓለም አቀፍ ቅጥር አቻ ግመታና የብቃት ሰነድ ለማግኘት ያግዛሉ ብለዋል።

ማዕቀፉ አንድ ምሩቅ ባለዲግሪ ነው ለማለት ማሟላት የሚገባውን መመዘኛ በግልፅ ያስቀምጣል።

ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያውያን ምሩቃን ከሀገር ሲወጡ ከትምህርታቸው ውጪ ዝቅ ባለ ስራ ለመቀጠር ይገደዱ ነበር።

በሀይለሚካኤል አበበ


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top