በ2023 የአፍሪካን ሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥ እንዲሁም የነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራ ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው-የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ-መንበር አዛሊ አሱማኒ

1 Yr Ago
በ2023 የአፍሪካን ሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥ እንዲሁም የነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራ ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው-የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ-መንበር አዛሊ አሱማኒ

በ2023 የአፍሪካን ሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥ እና የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራን ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫዎች አድረግው እንደሚሰሩ ተመራጩ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ-መንበር አዛሊ አሱማኒ ተናገሩ።

በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ፀጥታ ለማረጋገጥ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚሰጠው ኢ-ፍትሃዊ የገንዘብ ድጋፍ እንዲስተካከል ጥሪ ያቀረቡት ደግሞ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት ናቸው። 

ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 36ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች መደበኛ ጉባዔ ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል። 

በጉባዔው መዝጊያ ላይ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ተመራጩ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ-መንበር የኮሞሮሱ ፕሬዚዳንት አዛሊ አሱማኒ፤ በ2023 አፍሪካ ሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥ እና የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራን ቀዳሚ አጀንዳ አድርገው እንደሚሰሩ ገልጸዋል። 

በኃላፊነት ዘመናቸው ሰላምና ፀጥታ እንዲሁም የልማት አጀንዳዎችን ማሳካት ትልቅ ፈተና ቢሆንም አፍሪካውያንን ወደ አንድነት በማምጣት ስኬታማ ስራዎችን እንደሚያከናውኑ እምነታቸውን ገልፀዋል። 

አፍሪካ ያላት የተፈጥሮ ሀብት በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ በኩራት የሚያቆማት መሆኑን ገልፀው፤ ሀብቷን ማልማትና የንግድ ትስስሯን በማጠናከር ሁለንተናዊ ልማቷን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል። 

በኃላፊነት ዘመናቸው የሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥ እንዲሁም አህጉራዊ የነፃ ንግድ ቀጣናውን ትግበራ ማሳለጥ ተቀዳሚ አጀንዳቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካ ድምፅ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲሰማ በፀጥታው ምክር ቤት አባል እንድትሆን መስራት ሌላው ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ ጠቅሰዋል። 

የብሉ ኢኮኖሚ ጉዳይ አፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑና የ2063 አጀንዳ ስኬት ትልቅ ሚና ስላለው በአሳ ምርት ላይ አተኩረው እንደሚሰሩ ገልፀዋል።  

አፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ፀጥታ ለማረጋገጥ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እየሰጠ ያለው የገንዘብ ድጋፍ መስተካከል እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት ናቸው ::  

በአፍሪካ መሰረተ ልማት ግንባታ ማስፋፋት፣ የነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራን ማፋጠን፣ 600 ሚሊዮን ህዝብ ኃይል እጥረት ባለባት አፍሪካ የኃይል አቅርቦትን መጨመር እንዲሁም ዲጂታላይዜሽን ቁልፍ የትኩረት ስራዎች እንደሆኑ ገልፀዋል።  

በአህጉሪቷ ያለውን መልከ ብዙ የፀጥታ ችግር በራሷ አቅም ለመቅረፍ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክን ጨምሮ የሰላም ማስከበር ጥረቶችን በማንሳት በቀጣናው የፀጥታ ኃይሎች ጥምረት ወደ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጡ አቅጣጫ ተቀምጧል ነው ያሉት። 

የአፍሪካ ፀጥታ ችግሮች በተለይም ሽብርተኝነት ለዓለም ከቀፉ ማህበረሰብ ስጋት ቢሆኑም በፀጥታው ምክር ቤት የሚሰጠው ድጋፍ አነስተኛና ኢ-ፍትሐዊ መሆኑን ገልፀዋል። 

ሽብርተኝነትን ለመከላከል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለአፍሪካ የሚሰጠው ድጋፍ ፍትሀዊ አይደለም ያሉት የኮሚሽኑ ሊቀ-መንበር ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ በቂ የገንዘብ ድጋፍ ሊቀርብ እንደሚገባ ጠይቀዋል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top