የቀደምት ስልጣኔ መገለጫ፣ የበርካታ ታሪክ እና ባህል ባለቤት የሆነችው ጅማ ከተማ በኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻ ከሆኑት ከተሞች ተርታ ተሰልፋለች።
ከተማዋ ያሏትን የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ለጎብኚዎች ለማሳለጥ ሸብ ረብ እያለች ትገኛለች።
የጅማ ከተማ የቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ነጂብ ራያ ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ "የከተማ አስተዳደሩ ከተማዋ ያላትን የቱሪዝም መዳረሻ አጉልቶ ለማውጣት፣ እንዲሁም ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የከተማ ውበት እና መሰረተ ልማት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው" ብለዋል።
የቢሮ ኃላፊው እንዳሉት፤ "በጥንቃቄ የተያዘው የጅማ ሙዚየም፣ የጅማ የመጨረሻው ንጉስ የሆኑትን የአባ ጅፋርን ታሪካዊ ቅርሶች እንዲሁም የቀደምት ኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህል እና ስልጣኔ ሰንዶ ያኖረ በመሆኑ ለታሪክ ወዳድ ጎብኚዎች ዓይነተኛ መዳረሻ ነው"።
የጅማ ሙዚየም ስራ አስኪያጅ እና አስጎብኚ ክብሩ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ጅማ ካሏት ታሪካዊ የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል የ40 ታሪካዊ መስጂድ እንዲሁም የአባጅፋር እና የሌሎች ንጉሳዊያን ቤተሰቦች መካነ ቅርሶች እንደሚገኙባቸው ተናግረዋል።
በቀድሞ ባለቤቶቻቸው ተከቦ የሚገኘው ስድስት ሜትር ርዝመት ያለው የንጉሥ አባ ጅፋር መካነ መቃብር መጎብኘት ያለበት ስፍራ መሆኑን አንስተው፤ በበቂ ሁኔታ ሳይተዋወቅ በመቅረቱ እምብዛም ትኩረት ሳያገኝ ቆይቷል ብለዋል።
በጥሩ ሁኔታ የተጠበቀውን ሙዚየም እና የጅማ የመጨረሻ ንጉስ የአባ ጅፋር መካነ መቃብርን ጨምሮ ከተማዋ ልዩ የሆኑ ባህላዊ፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርሶችን አዋህዳ መያዟ ለጎብኚዎች ተመራጭ ያደርጋታል።
በተመሳሳይ የ170 ዓመታት ዕድሜን የተሻገረው የጥንታዊው አፉርተማ መስጂድ (40 መስጂድ) ባለፉት ዓመታት ትኩረት ያላገኘ ነገር ግን አስደናቂ ታሪክ ያቀፈ በመሆኑ፤ በከተማ አስተዳደሩ አሁን ትኩረት ተሰጥቶት የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ዜጎች በሰፊው እንዲጎበኙት እንዲሁም እንዲያውቁት ሰፊ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
ጅማ እና አከባቢው የኢትዮጵያን ታሪክ እና ስልጣኔ ከትናንት ዛሬ አሻግሮ ለማየት ለሚሹ ሁሉ ትክክለኛ መዳረሻ መሆኑም ተመላክቷል።
በወጋየሁ ሙሉነህ