በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶችን አስቀድሞ የመከላከልና በአጥፊዎች ላይ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) አስታወቁ፡፡
አለም አቀፍ የፀረ ፆታዊ ጥቃት ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ በድሬዳዋ መከበር ጀምሯል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፤ በሴቶች እና ህፃናት ላይ የሚደርሰው ፆታዊ ጥቃት አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት ከማስከተሉ ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል።
ችግሩን አስቀድሞ የመከላከልና በአጥፊዎች ላይ ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን ተናግረዋል።
ህገ መንግስቱን እንዲሁም አለም አቀፍ የሴቶችና የህፃናት መብቶችን ለማስከበር አዳዲስ አሠራሮች ተዘርግተው የሚወሰዱ ህጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልፀዋል።
ጥፋት የሚያደርሱ ሰዎችን በዘመናዊ የመረጃ አያያዝ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎችን በማጠናከር አስተማሪና ወሳኝ ቅጣት እንዲያገኙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ችግሩ የደረሰባቸው ህፃናትና ሴቶች ሁለገብ የህክምና፣ የህግ እና ሌሎች የአንድ ማዕከል አገልግሎቶችና የህፃናት ችሎት በማቋቋም ቀጣይ ህይወታቸው የተሳካ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በተለይ ከአለም ባንክ እና ከሌሎች አለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለጥቃት የተጋለጡ ሴቶች በኢኮኖሚና በማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው እንዲጎለብት እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
እነዚህን ጅምር ስራዎች ማጠናከርና ችግሩን መከላከል ለአንድ ተቋም ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉንም ዜጎች በተለይም የወንዶችን የተቀናጀ ርብርብና ድጋፍ ይጠይቃል ነው ያሉት።
በዛሬው ዕለት በድሬዳዋ መከበር የጀመረውና እስከ ታህሳስ 1/2017 ዓ.ም በሚዘልቀው የፆታ ጥቃት አለም አቀፍ ቀን የተጀመሩ ተግባራትን በህዝባዊ ንቅናቄ ለማጀብ መደላድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
በአከባበሩ ላይ የተሳተፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፈትህያ አደን በበኩላቸው የሴቶችና ህፃናትን ሰብዓዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ህገ መንግስታዊ መብቶች እንዲከበሩ የተቀናጀ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በአስተዳደሩ በሁሉም መስክ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራዎች በትኩረት መሰራታቸው መሠረታዊ ለውጦች እንዲመዘገቡ ቢያስችልም አሁንም በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ሙሉ በሙሉ የማስቆም ስራ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።
በድሬዳዋ አስተዳደር በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል ከፍትህ እና ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ በመሆኑ የተሻለ ለውጥ እየተመዘገበ ነው ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሁክሚያ መሐመድ ናቸው።
"የሴቷ ጥቃት የኔም ነው፤ ዝም አልልም" በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በድሬዳዋ መከበር በጀመረው አለም አቀፍ የፀረ-ፆታዊ ጥቃት ቀን ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ዘሓራ ሁመድ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የዘርፉ አመራሮች፣ የአለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ተወካዮች ተሳታፊ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።