የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የአልጀሪያ ቴክኒካዊ የመረጃ ተቋም ትብብራቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ተስማሙ

1 Day Ago 66
የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የአልጀሪያ ቴክኒካዊ የመረጃ ተቋም ትብብራቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ተስማሙ

የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የአልጀሪያ ቴክኒካዊ የመረጃ ተቋም በቴክኒካዊ የመረጃ ዘርፍ እያደረጉት ያለውን የትብብር ማዕቀፍ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ተስማምተዋል፡፡

በአልጀሪያ ቴክኒካዊ የመረጃ ተቋም ዳይሬክተር ጀነራል ከሊፋ ሚስባሃ የተመራ የልዑካን ቡድን አዲስ አበባ የገባ ሲሆን፤ የልዑካን ቡድኑ አዲስ አበባ ሲገባ በብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል እንደተደረገለት አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ለኢቢሲ በላከው መረጃ አመልክቷል፡፡

የልዑካን ቡድን አባላቱ ከብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጋር ረጅም ግዜ በዘለቀው የትብበር ስራዎች በወቅታዊው፣ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ በስፋት የተወያየ ሲሆን፤ ሁለቱ አቻ የመረጃ ተቋማት በቴክኒካዊ የመረጃ ዘርፍ  እያደረጉት ያለውን የትብብር ማዕቀፍ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር መስማማታቸውን ተመላክቷል፡፡

ውይይቱን የመሩት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የገጠማትን የፀጥታ ተግዳሮቶች በውይይት ለመፍታት ቅድሚያ ሰጥታ እየሰራች ስለመሆኑና የቀጠናውን መረጋጋት ለማረጋገጥ እየሰራች እንደምትገኝ፤ በተጨማሪም በሠላማዊ አማራጮች የባህር በር ተደራሽነት ለማግኘት የጀመረቻቸውን እንቅስቃሴዎች ለልዑካን ቡድኑ አብራርተዋል፡፡

የአልጄሪያ ቴክኒካዊ የመረጃ ተቋም ዳይሬክተር ጀነራል ከሊፋሀ ሚስባሃ በበኩላቸው ተቋማቸው ከአገልግሎት መስሪያ ቤቱ ጋር የጀመራቸውን የመረጃ ልውውጥ ስራዎችንና የቴክኒካዊ መረጃ የትብብር ማዕቀፎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የልዑካን ቡድን አባላቱ ከውይይቱ በኋላ ከብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ታዜር ገ/እግዚአብሄር እና ከሌሎች የተቋሙ አመራሮች ጋር በመሆን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝቱ ወቅትም የአልጀሪያ ቴክኒካዊ የመረጃ ተቋም ዳይሬክተር ጀነራል ከሊፋ ሚስባሃ ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብት አቅም ማድነቃቸውንና ግድቡ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን፤ ለጎረቤቶቿም ጭምር የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ በማቅረብ ግልጋሎት የሚሰጥ የትብብር እና አብሮ የመልማት ምዕራፍ የሚከፍት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት ለልዑካን ቡድኑ ያብራሩ ሲሆን፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም አንዱና ግንባር ቀደሙ መገለጫ መሆኑን እና ከሀገሪቱ አልፎ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት እንዲሁም ለቀጠናው የሚያበረክተው አዎንታዊ ሚና ከፍተኛ እንደሆነ መናገራቸውን የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢቢሲ የላከው መረጃ ያመለክታል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top