የሕዝብን ምሬት የሚያበዙ የአፈጻጸም ክፍተቶችን ለማረም ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል እንደሚደረግ ተገለፀ

5 Days Ago 138
የሕዝብን ምሬት የሚያበዙ የአፈጻጸም ክፍተቶችን ለማረም ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል እንደሚደረግ ተገለፀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰጡትን ማብራሪያ አስመልክቶ ከኢቲቪ ዳጉ ፕሮግራም ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

የምክር ቤቱ ውሎ ብዙ ግርታዎች እና ብዥታዎች የጠሩበት ነው ያሉት አመራሮቹ፤ በቀጣይም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በመንግስት ዕቅዶች አፈጻጸም ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እና ክትትል እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ስትተገብረው የነበረው ሪፎርም ዘርፈ ብዙ ለውጥ እያመጣ እንደሆነ ገልጸው፤ ግብርና ከፍተኛ ለውጥ እንዳመጣ እና በቀጣይም ኢትዮጵያ የምትሻውን ዕድገት እንድታስመዘግብ ዘርፉ ትልቁን ድርሻ ይዞ እንደሚቆይ ገልጸዋል፡፡

የከተማ መሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ እሸቱ ተመዝገን (ዶ/ር) እንዳሉት የከተማ ልማትን በተመለከተ እየተሠሩ ያሉት ሥራዎች እጅግ አመርቂ ውጤት ያስገኙ ናቸው፡፡  

ከአዲስ አበባ ጀምሮ ወደ ክልሎች እየሰፋ ያለው የኮሪደር ልማትም ከተሞቻችን ለዜጎቻቸው ምቹ እንዲሆኑ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ መሰረተ ልማትን በተመለከተም ተጨማሪ በጀት ሳይመደብ እየተሠሩ ያሉ የከተማ መሰረተ ልማቶች የከተሞችን ዘመናዊነት እያሻሻሉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በኮሪደር ልማቱ አፈጻጸም ሂደት እንከኖች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ አውስተው፤ ችግሮቹን አርሞ መሄድ እንደሚያስፈልግና ምክር ቤቱም ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ እርማት እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡

እየተጀመረ ያለው የገጠር ኮሪደር ልማት በዚህ ወቅት መሆኑም በከተማ ካለው አፈጻጸም ተምረን የተሻለ ውጤት የምናስመዘግብበት እንዲሆን ያደርገዋል ብለዋል፡፡

የህዝብ ተወካዮች አማካሪ ምክር ቤት አባል አብረሃም በርታ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኑሮ ውድነትን ለመቅረፍ እየተደረገ ያለው ጥረት ጥሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በየቦታው የተከፈቱት የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦ አበረታች መሆኑን የጠቀሱት አብረሃም በርታ (ዶ/ር)፤ ምርት እና ምርታማነትን በማሻሻል ለኑሮ ውድነቱ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ 

ሀገራችን ተረጋግታ ወደ ልማት እንድታተኩር ሰላም አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ሁሉም በትኩረት መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ 

ለሰላም መደፍረሱ ምክንያቶች ዛሬ የተፈጠሩ ጉዳዮች እንዳልሆኑ ጠቅሰው፤ ያደሩ ችግሮቻችንን በመቅረፍና ቀጣዩ ሰላማችንን ለማረጋገጥ ደግሞ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እየሠራቸው ያሉትን ሥራዎች ማገዝ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በዚህ ዓመት ያለው ምርት በጣም ተስፋ ሰጪ እንደሆነ የጠቀሱት ደግሞ የንግድ እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ አቶ አስቻለ ላምሬ ናቸው፡፡

አቶ አስቻለ ግብርና ለኢትዮጵያ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ምክር ቤቱ ከዘር እስከ ምርት አሰባሰብ ያለውን ሁኔታ በጥብቅ እየተከታተለ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ሦስት ወራት ከግብርናው ዘርፍ 1.5 ቢሊዮን መገኘቱን የገለጹት አቶ አስቻለ፤ የምክር ቤቱ አባላት ታች ወርደው እንዳዩት በስንዴ፣ በሩዝ፣ በቡና እና በሌሎች ሰብሎች መሬት ላይ ተጨባጭ ተስፋ እንዳለ ጠቅሰዋል፡፡

የየሸቀጦችን ነጻ ዝውውር ለማሳለጥ በክልል ያሉ የተለያዩ ኬላዎች እንዲነሱ መደረጉን ጠቁመው፤ ጤናማ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር እና ወጪ ንግድ በጥራትም በብዛትም እንዲሻሻል በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የገበያውን ሁኔታ እያዛባ ያለው የምርት ማነስ ብቻ ሳይሆን የንግዱን መሥመሩን የያዙት አካላት እንደሆኑና እነዚህ ደግሞ በመንግሥት መዋቅር ውስጥም የተወሸቁ ጭምር መናቸውን ገልጸዋል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ህገወጦችን ለይቶ እርምጃ መውሰዱን አጠናክሮ መቀጠሉን የገለጹት አቶ አስቻለ፤ በህገወጥ መንገድ ገበያውን የሚያዘቡት ላይ በሚደረገው ቁጥጥር እና የሚወሰደው እርምጃ እንዲሳካ ሕዝቡ መተባበር አለበት ብለዋል፡፡

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top