የአሜሪካ ምርጫ በትራምፕ እና በሃሪስ እኩል ነጥብ ቢጠናቀቅ ምን ይፈጠራል?

1 Day Ago 132
የአሜሪካ ምርጫ በትራምፕ እና በሃሪስ እኩል ነጥብ ቢጠናቀቅ ምን ይፈጠራል?
የዴሞክራት ፓርቲ ፕሬዚደንታዊ እጩ ካማላ ሃሪስ እና የሪፐብሊካን ብርቱ ተፎካካሪያቸው ዶናልድ ትራምፕ በዚህ ምርጫ ባላቸው ፉክክር የተነሳ እኩል ነጥብ ቢያመጡ ምን ይሆን መጨረሻው የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ።
 
እንደዚህ አይነት አጋጣሚዎች የመከሰት እድላቸው ሰፊ ባይሆንም አይከሰቱም ማለት ግን አይቻልም።
 
አሜሪካውያን በእነሱ አቆጣጠር ከህዳር 5 ምርጫ በፊት ቀደም ሲል የእኔ ሚሉትን ወስነው እየጠበቁ የነበረ ቢሆንም፤በአሜሪካ ምርጫ ታሪክ ውስጥ እስከመጨረሻው ሰዓት የማይወስኑ እና በመጨረሻ ሀሳብ የሚቀይሩ “ስዊንግ ስቴትስ” በመኖራቸው ውጤቶችን ለመገመት አዳጋች ነው።
 
በአሜሪካ ሥርዓት ማን ፕሬዚደንት እንደሚሆን የሚወስነው የብሔራዊ የህዝብ ድምጽ ሳይሆን 538 አባላት ያሉት "የምርጫ ኮንግረስ" ነው።
 
የአሜሪካን ሕግ ይህንን ሲያብራራ ሃሪስ እና ትራምፕ የ270 መራጮች አብላጫ ድምፅ ካላገኙ ወይም እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ ካልቻሉ የአሜሪካ ሕገ መንግስት ኮንግረስ የመወሰን ሚና ይኖረዋል ይላል።
 
ይህ ሲሆን አዲስ የሚመረጠው የተወካዮች ምክር ቤት በጥር ወር ፕሬዚደንቱን ይመርጣል፤ሴኔቱ ደግሞ ተሰብስቦ ቀጣዩን ምክትልፕሬዚደንት ይወስናል የሚል ሕግ ሰፍሮ ይገኛል።
 
ምሳሌ ዲሞክራት ፓርቲ እጩ የሆኑት ካማላ ሃሪስ በዊስኮንሲን፣ሚቺጋን እና ፔንስልቬንያ ግዛቶች ውስጥ ቢያሸንፉ፣ የሪፐብሊካኑ እጩ እና የቀድሞ የአሜሪካን ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ ጆርጂያ፣አሪዞና፣ኔቫዳ እና ሰሜን ካሮላይና እንዲሁም በኔብራስካ ውስጥ ባለ አንድ የምርጫ ወረዳ ቢያሸንፉ እኩል ድምጽ የማምጣት እድል ሊፈጠር ይችላል።
 
በዘመናዊው የአሜሪካ የምርጫ ታሪክ ይህ ጉዳይ ያልተደረገ እና ያልተከሰተ ቢሆንም ዘንድሮ እድሉ ሰፊ ስለመሆኑ እየተነገረ ነው።
ለመጨረሻ ጊዜ ኮንግረስ ፕሬዚደንቱን እንዲመርጥ የተገደደው በአውሮፓውያኑ 1800 ምርጫ ሲሆን ይህም ቶማስ ጀፈርሰንን ከፕሬዚደንት ጆን አዳምስ ጋር ያገናኘው ምርጫ ነበር።
 
በጊዜው ምክር ቤት ውስጥ ያሉ ሕግ አውጪዎች ለመስማማት በከፍተኛ ሁኔታ የተሟገቱ ሲሆን በመጨረሻም ቶማስ ጀፈርሰንን በ36ኛው ድምጽ መስጫ መርጠው ፕሬዚደንት አድርገዋል።
 
ታዲያ ይህ ታሪክ አሁን ከተደገመ እና የምክር ቤቱ ድምጽ አስፈላጊ ከሆነ በአውሮፓውያኑ ጥር 6 ቀን 2025 ፕሬዚደንቱን የሚሰይም ይሆናል።
 
ከዚህ ባለፈ ግን የአሜሪካን የድምፅ ሂደት እግር በእግር መከታተል ቢቻል እንኳን ምርጫውን መወሰን የሚችለው ኢሌክቶራል ቮት ነውና እስከመጨረሻ አሸናፊውን ለመወሰን አስቸጋሪ መሆኑ አይቀሬ ነው።
 
እናንተስ በዚህ ዓለምን እያነጋገረ ባለው የአሜሪካ ምርጫ ማን የሚያሸንፍ ይመስላችኋል?
 
በናርዶስ አዳነ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top