በቁጭት የጀመርነውን የዓለም ከተሞች ከደረሱበት የመድረስ ግስጋሴያችንን እናፋጥናለን፡- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

1 Mon Ago 232
በቁጭት የጀመርነውን የዓለም ከተሞች ከደረሱበት የመድረስ ግስጋሴያችንን እናፋጥናለን፡-  ከንቲባ አዳነች አቤቤ
በቁጭት የጀመርነውን የዓለም ከተሞች ከደረሱበት የመድረስ ግስጋሴያችንን እናፋጥናለን እንጂ ፈፅሞ አንቆምም፤አንዘገይምም ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አደነች አቤቤ ገለጹ።
 
ከንቲባዋ በአራት ቀናት የማሌዢያ ቆይታቸው ኳላ ላምፑር፣ሳይበርጂያ እና ፑትራጂያ የተባሉ ከተሞችን መጎብኘታቸውን ገልጸዋል።
 
በቆይታቸው ነባር ከተሞቻቸውን ከማደስ በተጨማሪ አዳዲስ ከተሞችንም እየገነቡ መሆኑን መመልከታቸውን ከንቲባዋ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ፅሑፍ ገልጸዋል።
 
ነባሮቹም ሆኑ አዲስ የሚገነቡ ከተሞቻቸውን ልዩ የሚያደርጋቸው ነዋሪዎች እንቅስቃሴ የሚያደርጉባቸውና ጤናቸውን ለመጠበቅ የሚገለገሉባቸው ሰፋፊ የህዝብ መዝናኛዎችን፣ የኮንቬንሽንና የገበያ ማዕከላትን፣መናፈሻዎችን እና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን መገንባታቸው ነው ብለዋል።
 
በተጨማሪም ሰው ሰራሽ ወንዝ እና ሃይቆች በመፍጠር ንጹህ ምቹ እና ለኑሮ ተስማሚ የሆነ አካባቢን መገንባታቸው እንዲሁም ከአጠቃላይ የከተማው ስፋት 38 በመቶ የሚሆነውን ለአረንጓዴ ልማት በማዋል ትልቅ ስራ መስራታቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
 
ይህም በቂ አይደለም በማለት፣ ስራው እንደ ቅንጦት ሳይሆን ከመታመም በፊት መከላከል አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ እና የጤና አጠባበቅ ወሳኝ በመሆኑ ትልቅ ትኩረት ሰጥተው በመስራት ላይ መሆናቸው ከንቲባዋን እንዳስገረማቸው ገልጸዋል።
 
በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ዘግይተንም ቢሆን የጀመርነው ስራ እየፈጠነ ነው ብለዋል ከንቲባ አዳነች።
 
አክለውም እኛ ከእነሱ አንፃር በተሻለ ሁኔታ ክረምትና በጋ ማሞቂያ እና ማቀዝቀዣ የማያስፈልገው፣ ወጥነት ያለው ተስማሚ የአየር ንብረት እና ውሃ፣ትልቅ የሰው ሀይል እንዲሁም ሰፊ መሬት ያለን ሲሆን ይህን እምቅ አቅማችንን በመጠቀም ከተማችንን ለመለወጥ በመስራት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
 
በተለይ በአዲስ አበባ የአረንጓዴ ሽፋናችን በአምስት ዓመት ውስጥ ከነበረበት 2.8 በመቶ ወደ 20 በመቶ ማድረስ መቻሉንም ገልጸዋል።
 
አያይዘውም፤ህዝባችንን በማስተባበር በጀመርነው የ24 ሰዓት 7 ቀናትየስራ መርሃግብር የከተማችንን ነዋሪዎች ጤና ለመጠበቅ ወሳኝ የሆነውን ንጹህ እና ለኑሮ ተስማሚ የሆነ አካባቢ መፍጠርን፣ ነዋሪዎች እንቅስቃሴ የሚያደርጉባቸው ክፍት ቦታዎችን ማዘጋጀትን፣ ለእግረኛ መንገዶች ትኩረት በመስጠት ምቹና ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶች መገንባትን፣ ፓርኮችን እና መናፈሻዎችን ማስፋፋትን፣ የአረንጓዴ ልማት ሽፋናችንን አሁን ካደረስነው በላይ ማሳደግን፣ የህፃናትና ታዳጊዎች የመጫወቻ ስፍራዎችን ማስፋፋትን እንዲሁም የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን በብዛት መገንባትን አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል ብለዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top