በኦሮሚያ ክልል የአፈር አሲዳማነትን ለመቀነስ የኖራ ምርትን በእጥፍ ለማምረት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

5 Days Ago 108
በኦሮሚያ ክልል የአፈር አሲዳማነትን ለመቀነስ የኖራ ምርትን በእጥፍ ለማምረት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

የአፈር አሲዳማነትን ለመቀነስ የኖራ ምርትን በእጥፍ ለማምረት እየሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን የጉደር ኖራ ፋብሪካና በክላስተር የተሰሩ ሰፋፊ ሰርቶ ማሳያ ስራዎችን ለማስተዋወቅ ሀገር አቀፍ የመስክ ጉብኝት ተደርጓል፡

በጉብኝቱ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከክልልና ከወረዳ ግብርና ቢሮዎች፣ ከግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቶች፣ ከአፈር ምርምር ማዕከላት የተውጣጡ አመራሮችና ባለሙያዎች የጉዳር ኖራ ፋብሪካ ማዕከልን ተመልክተው የልምድ ልውውጥ አድርገዋል።   

በዚሁ ወቅት የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኤልያስ ከድር፤ ጉዳር ኖራ ፋብሪካ የማምረት አቅሙን በእጥፍ በማሳደግ 196 ሺህ የነበረውን ምርት ወደ 400 ሺህ ኩንታል ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አፈርን ማከም የአማራጭ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታ ነው ያሉት ምክትል ኃላፊው፣ የክልሉ መንግስት በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የተጎዳውን አፈር አክሞ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

በመስክ ጉብኝቱ ወቅት የአፈር መሸርሸር በአገሪቷም ሆነ በክልሉ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የተገለፀ ሲሆን ይህንን ችግር ለመቅረፍ የኦሮሚያ ክልልም ሆነ የፌዴራል መንግስት የመሬት ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተመላክቷል።  

በኦሮሚያ ክልል 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር የእርሻ መሬት በአፈር መሸርሸር የተጎዳ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

የጉዳር ከተማ የማምረት አቅም እያደገ መምጣቱንና የኖራ ፋብሪካ ማዕከላትን ማስፋት እንደሚገባ በመስክ ጉብኝቱ የተሳተፉ አመራሮች ተናግረዋል።

በጀማል ነጌሶ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top