የኢትዮጵያውያን የወል ትዝታ፣ የአፍሪካ ሕብረት የብሥራት ድምጽ

4 Days Ago 144
የኢትዮጵያውያን የወል ትዝታ፣ የአፍሪካ ሕብረት የብሥራት ድምጽ

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የኢትዮጵያ የበኩር ድምጽ ነው። ኢትዮጵያውያን የማይረሷቸውን የጋራ ትዝታዎች የተጋሩበት የትዝታቸው መስኮት። የልጆች ዓለም የአባባ ተስፋዬ ምክሮችና ተረቶች፣ ዘወትር ቅዳሜ የሚተላለፈው ታላቁ ፊልም፣ የሀገራችን ስመ ጥር አርቲስቶችን ያስተዋወቀው 120 ፕሮግራም፣ የኢትዮጵያውያንን ቀለም የሚያደምቀው ሕብረ-ትርዒት፣ ጉምቱ ኢትዮጵያውያንን ያስተዋወቀው አውደ ሰብ፣ ቤተሰብን የሚያሰባስቡት የእሁድ ዝግጅቶች የኢትዮጵያውያን የወል ትዝታዎች ናቸው። እነዚህን ዝግጅቶች ደግሞ ከሽኖ ለሕዝብ ሲያቀርብ የነበረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ነው። 

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የብዙዎች ባለውለታ ነው። ህጻናት ምክር ሰምተው አድገውበታል። የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች አቅማቸውን አሳይተውበታል። ጎልማሶች እና አረጋውያን ትምህርት እና መረጃ አግኝተውበታል። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉት ሚዲያዎች ሁሉ መሰረት የጣለ የኢትዮጵያ ሚዲያ ኢንዱስትሪ ፈር ቀዳጅም ሆኗል። 

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላለፉት ስድሳ ዓመታት በባህል መስኮትነት፣ በትምህርት፣ በጥበብ መድረክነት፣ በሀገር ግንባታ ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን አገልግሏል። የኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ዐበይት ሁነቶች እና መታጠፊያዎች የተበሰሩት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ነው። 

አፍሪካውያን የነጻነት ጥያቄያቸውን የሚያስተጋቡበት ልሳን ባልነበራቸው በዚያ ዘመን፤ የሕብረታቸውን ድምጽ የሚያሰሙበት መገናኛ ባጡበት በዚያን ጊዜ ድምጽ የሆናቸውም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ነው። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የአፍሪካውያን ሕብረት ብሥራት የተሰማበት ሚዲያ ነው፤ አፍሪካውያን ሕብረታቸውን እንዲያጸኑ ተመክሮበታል። ኢቲቪ አፍሪካውያን በሕብረት ሆነው የተሟላ ነጻነታቸውን እንዲያውጁ ድምጽ ሆኖአቸዋል፤ የአፍሪካውያን የነጻነት ብሥራትም ተሰምቶበታል። 

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዛሬ ኢቲቪ ዜና፣ ኢቲቪ መዝናኛ፣ ኢቲቪ አፋን ኦሮሞ፣ ኢቲቪ የልጆች ዓለም፣ ኢቲቪ ቋንቋዎች እና ኢቲቪ ፓርላማ በተሰኙ ስድስት ቻናሎች ዝግጅቶቹን ወደ ተመልካቾቹ ያቀርባል። ኢቲቪ አማራጮችን አስፍቶ፣ ብዝኃ ቋንቋን አቅፎ የኢትዮጵያውያን ድምጽ ለመሆን እየሠራ ነው። 

ኢቢሲ እንደ አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ፣ አፋርኛ እና ሶማልኛ ባሉት የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ኢትዮጵያን ይተርካል። እንደ እንግሊዝኛ፣ ዓረብኛ እና ፈረንሳይኛ ባሉት የውጭ ቋንቋዎች ኢትዮጵያን እና አፍሪካን ይተርካል። 

የጥበብ፣ የዕውቀት እና የመረጃ ቤት የሆነው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲን ኮርፖሬሽን "ኢቢሲ ወደ ይዘት" በሚል መሪ ቃል የኢትዮጵያን ኅብረ ብሔራዊነት የሚያደምቁ ዝግጅቶችን ለማቅረብ ሥራ ጀምሯል። በአዳዲስ የይዘት ለውጦች የኢትዮጵያውያንን እና የኢትዮጵያን ፍላጎት እና ህልም ለማሟላት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። የኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ መተረኪያ መስኮት ለመሆን እየሠራ ነው። 

ኢቢሲ "25፣ 60፣ 90" በሚል ፕሮጀክት የኢትዮጵያውያንን የወል ትርክት ለማጉላት እየሠራ ይገኛል። ለመሆኑ 25፣ 60፣ 90 ምንድን ነው? በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ኤፍ.ኤም ሬዲዮ ኤፍ.ኤም አዲስ 97.1 ሃያ አምስት ዓመቱ ነው፤ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ቴሌቪዥን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን 60 ዓመት ሞላው፤ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሬዲዮ የኢትዮጵያ ሬዲዮ 90ኛ ዓመቱ ነው። ኢቢሲ በኢትዮጵያ ብሮድካስት ሚዲያ ታሪክ ፈር ቀዳጅ እንደመሆኑ፤ ኢትዮጵያውያንን በማገልገል ግንባር ቀደም ሆኖ ለመውጣት፣ ከዚያም አልፎ እንደ ትናንቱ የአፍሪካ ድምጽ ለመሆን ይሠራል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top