የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተሳካ ሀገራዊ ምክክር እንዲኖር በትጥቅ ትግል ላይ የሚገኙ አካላት ያላቸውን አጀንዳ በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
በትጥቅ ትግል እየተፈተነ የሚደረግ ምክክር በኢትዮጵያ ብቻ የሚካሄድ አለመሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፤በኮሎምቢያ በትጥቅ ትግል ወቅት የተደረገውን ውጤታማ ምክክር ለአብነት አንስተዋል፡፡
ሁሉም ማህበረሰው ያለው ጥያቄ እና አጀንዳ እንዲነሳ እንፈልጋለን ያሉ ሲሆን፣ኮሚሽኑ በቀጥታም ሆነ በውክልና ተሳትፎ ሃሳብ ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ችግሮቻችንን በጋራ በመቅረፍ ለመጪው ትውልድ ተስፋን መሰነቅ ይገባል ያሉት ኮሚሽነሩ፤የታጠቁ ኃይሎች ይህንን እድል በመጠቀም የተሻለች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የምክክሩ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አጀንዳ የማሰባሰቡ ስራ በሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ ምሁራን እና ሲቭክ ማህበራት አማካኝነት በተለያዩ አካባቢዎች መቀጠሉንም አያይዘው ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትናንትናው ዕለት በምክር ቤቱ ተገኝተው በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ መንግስት ግጭቶች በሰላም እንዲፈቱ ቅድሚያ ሰጥቶ መስራቱን ገልጸው፤አሁንም ያለን አቋም የትኛውም አይነት አለመግባባት በሰላም እንዲፈታ ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ከኃይል አማራጭ ይልቅ የሰላም አማራጭ ውጤቱ ከፍተኛ ነው፤ ሃሳብ አልባ ትግል ፍሬ የለውም ማለታቸውም እንዲሁ፡፡