ስሎቬኒያ በባለብዙ ወገን መሥኮች ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመሥራት እንደምትፈልግ ገለፀች

5 Days Ago 144
ስሎቬኒያ በባለብዙ ወገን መሥኮች ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመሥራት እንደምትፈልግ ገለፀች

ስሎቬኒያ ከኢትዮጵያ ጋር በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን መሥኮች በጋራ አብሮ ለመሥራት እንደምትፈልግ አስታወቀች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ከስሎቬኒያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭና የአውሮፓ ጉዳዮች ሚኒስትር ታንያ ፋጆን ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ላይ ዶ/ር ጌዲዮን ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለው ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ የፈጠረ በመሆኑ የስሎቬኒያ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲሠማሩ ጠይቀዋል።

ስሎቬኒያ የአውሮፓ ሕብረት አባል እና ተለዋጭ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አባል መሆኗ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ሕብረት እና ከተመድ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር መልካም ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ከስሎቬኒያ ጋር በቴክኖሎጂ ሽግግር በተለይም በግብርና እና በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ትብብሯን ማጠናከር እንደምትፈልግ ዶ/ር ጌዲዮን ገልጸዋል።

ዶ/ር ጌዲዮን ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ያላትን ጉልህ ሚና ገልጸው፤ በድሕረ አትሚስ የኃይል ሥምሪት ውሳኔ፣ ሒደት እና አተገባበር ላይ ልዩ ጥንቃቄ እንደሚያሻው መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።  

እስካሁን በቀጣናው አልሸባብን በመዋጋት ረገድ የኢትዮጵያ ሚና የማይተካ እንደነበር በማስታወስ የተገኙ ድሎች እንዳይቀለበሱ ከዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ጋር በትብብር መሥራቷን እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።

ታንያ ፋጆን በበኩላቸው፤ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን መሥኮች በጋራ አብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።

በተለይም በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በውኃ አጠቃቀም፣ በግብርና መስክ በተለይም በንብ ማነብ ያላትን ልምድ እና ተሞክሮ እንዲሁም በሰው ሰራሽ አስተውሎት ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top