የኤ350-1000 አውሮፕላን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬታማ ጉዞ ማሳያ ነው - ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ

1 Mon Ago 231
የኤ350-1000 አውሮፕላን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬታማ ጉዞ ማሳያ ነው - ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ

የኤ350-1000 አውሮፕላን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬታማ ጉዞ ማሳያ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 124 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ማዘዙን በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡

ይህም አየር መንገዱ በተፋጠነ የስኬት ጉዞ ላይ መሆኑን የሚያመላክት እርምጃ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

በዚህም አየር መንገዱ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ኤ350-1000 የመንገደኞች አውሮፕላንን ትናንት ከኤርባስ ኩባንያ የተረከበ ሲሆን፤ በዛሬው እለትም አውሮፕላኑ አዲስ አበባ ገብቷል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፤ ኤ350-1000 አውሮፕላን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬታማ ጉዞ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አየር መንገዱ በአቪየሽን ዘርፉ እያሳየ ያለውን ስኬት ከኢትዮጵያ ባሻገር ለመላው አፍሪካዊያን ኩራት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፤ ኤ350-100-አውሮፕላን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለጀመረው የእድገት ጉዞ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህም በአፍሪካ የአቪየሽን ኢንደስትሪ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ነው ያበራሩት፡፡

አየር መንገዱ የላቀ የደንበኞች አገልግሎት እንዲሰጥ ከማድረጉም በላይ በዘርፉ ያለውን ተወዳዳሪነት ይበልጥ የሚያሳድግ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው አክለውም የኤ350-1000 አውሮፕላን ከኢትዮጵያ ባለፈ ለአፍሪካ አቪየሽን ዘርፍ አዲስ ተስፋን የሰነቀ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

በኤር ባስ ኩባንያ የአፍሪካ ንግድ ምክትል ፕሬዝዳንት ሃዲ አኩም በበኩላቸው ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙለት ኤ350-1000 አውሮፕላን አየር መንገዱ በቀጣይ ይበልጥ የተሻለ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችለው መግለፀቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

አየር መንገዱ አውሮፕላኑን ሙሉ በሙሉ በራሱ አቅም ማብራርና መቆጣጠር መቻሉ ደግሞ በሰው ኃይል ልማት ዘርፍ ያለበትን ደረጃ እንደሚያሳይ አብራርተዋል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top