ኦሮምኛን አቀላጥፈው የሚናገሩት ጃፓናዊቷ የቦረና ኦሮሞ የመልዩ ጎሳ አባል በኦዳ ቡሉ ስርዓት ለመካፈል ምስራቅ ቦረና ዞን አሬሮ ወረዳ ገጠራማ ስፍራ ተገኝተዋል፡፡
በጃፓን ወላጆቿ ያወጡላቸው ስም ቺካጌ ኦባሱሌት ይሁን እንጂ፤ ከቦረና ኦሮሞ ማንነት ጋር ተዋህደው የመልዩ ጎሳ አባል ከሆኑ በኋላ ሎኮ ዱባ ካሩ (ዶ/ር) በሚል ስማቸው ይታወቃሉ፡፡
ከ20 ዓመት በፊት በቦረና ምድር ተገኝተው ለሁለተኛ ድግሪ (ማስተርስ) ጥናታዊ ፅሁፋቸው ሲሰሩ ከቦረና ህዝብ ጋር በእጅጉ እንዳስተዋወቃቸው ይገልፃሉ፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ ቦረና ጋዩ በሚባል የመልዩ ጎሳ በሚገኙበት ስፍራ ማረፊያቸው ያደረጉት ጃፓናዊቷ፤ ኦሮምኛ ቋንቋን በዚሁ ስፍራ መማራቸውን ይገልጻሉ፡፡
ከቦረና ህዝብ ባህል ጋር የተቆራኙት ሎኮ ዱባ ካሩ (ዶ/ር) የቦረና የመልዩ ጎሳ አባልም መሆን ችለዋል፡፡
የ3ኛ ዲግሪያቸውን (ፒኤችዲ) በቦረና ባህልና ታሪክ ላይ ነው ጥናታዊ ፅሁፋቸውን የሰሩት ጃፓናዊቷ፤ ይህ አጋጣሚ ሰፊውን የቦረና ምድር በመዘዋወር ከባህሉና ታሪኩ ጋር እንዲተዋወቁ ዕድል ፈጥሮላቸዋል፡፡
ከ100 በላይ የገዳ ስርዓት አዋቂዎች ጋር በመገናኘት ከ560 ዓመታት በላይ ያስቆጠረውን የቦረና የገዳ ስርዓት ከስር መሰረቱ መማራቸውን ያነሳሉ፡፡
በዚህም በእንግሊዘኛና በጃፓንኛ ቋንቋ መፅሀፍ በማሳተም ስርዓቱን ለዓለም ለማስተዋወቅ አሻራቸውን አስቀምጠዋል፡፡
ከ3ኛ ዲግሪያቸው በኋላ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ተቀጥረው ሰርተዋል፡፡ አሁን ላይ በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የባህልና የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ናቸው፡፡
ኦዳ ሳያድሩ የቦረና ባህልና ታሪክን መረዳት ስለሚያስቸግር የኦዳ ቡሉ ስርዓት በሚደረግበት አሬሮ ወረዳ መገኘታቸውን ይገልፃሉ፡፡
ኦዳ ቡሉ የቦረና ኦሮሞ የገዳ ስርዓት አካል ሲሆን ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበትና የሚለመንበት ነው፡፡
በስርዓቱ የቦረና ኦሮሞ በህይወት ዘመናቸው አንዴም ቢሆን መገኘት እንደሚኖርባቸው አባገዳዎቹ የሚገልፁ ሲሆን፤ ጃፓኒዊቷ ሎኮ ዱባ ካሩም (ዶ/ር) በስፍራው ተገኝተው እንደ አንድ የጎሳ አባል ስርዓቱን እየተካፈሉ ይገኛሉ፡፡
በሙሉ ግርማይ