የፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋዬ ዳባ ከኮሪያ ሪፐብሊክ ፀረ-ሙስና እና ሲቪል መብቶች ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር ቹንግ ዩንግ ዩን ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ ሁለቱ አገራት የሙስና ወንጀል ከመከላከል፣ አጥፊዎችን ተጠያቂ ከማድረግ እና በወንጀል የተገኘ ሀብት ከማስመለስ አኳያ በጋራ በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።
ሚኒስትር ዴኤታው መንግስት በወንጀሎች ምርመራ፣ክርክርና የተመዘበሩ የሕዝብ እና የመንግስት ሀብት ከማስመለስ ረገድ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በዘርፉ ከኮሪያ ሪፐብሊክ ተቋማት ጋር ልምድ ለመለዋወጥና በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።
የባለሙያዎችን የምርመራና ክርክር ክህሎት ማሳደግ፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር ተግባራዊ በማድረግ እና በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘ ሀብት ማስመለስና ማስተዳደርን በተመለከተ በጋራ በትብብር ሊሰራባቸው ከሚገባቸው ጉዳዮች የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።
የኮሪያ ሪፐብሊክ ፀረ-ሙስና እና ሲቪል መብቶች ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር ቹንግ ዩንግ ዩን በበኩላቸው ተቋማቸው የሙስና ወንጀሎችን በመከላከል እና ለወንጀል ጠቋሚዎችና ምስክሮች ተገቢውን ከለላ በመስጠት ረገድ ውጤታማ ስራ ማከናወኑን ገልጸዋል።
ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በሙስና ወንጀል በመከላከል እና ተጠያቂነት በማስፈን ረገድ አብረው ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋዬ ዳባ ሙስናን ከመከላከልና አጥፊዎችን ተጠያቂ ከማድረግ ረገድ በሁለቱ አገራት ተቋማት መካከል የጋራ የትብብር ማዕቀፍ በማዘጋጀት እንደሚተገበር መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።