የኃይማኖት ተቋማት ፅንፈኝነትን ለማስወገድ በቁርጠኝነት መስራት አለባቸው - ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ

2 Days Ago 128
የኃይማኖት ተቋማት ፅንፈኝነትን ለማስወገድ በቁርጠኝነት መስራት አለባቸው - ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ

የኃይማኖት ተቋማት ለዓለም ፈተና እየሆነ ያለውን የፅንፈኝነትና የመከፋፈል እሳቤን ለማስወገድ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ ተናገሩ።

የሰላም ሚኒስቴር በዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ከሚገኘው ከመሐመድ ቢን ዛይድ ፎር ሁማኒቲ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ዓለም አቀፍ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ  በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።

በጉባኤው መክፈቻ የኢፌዴሪ የፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ጨምሮ የሠላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም፣ የመሐመድ ቢን ዛይድ ፎር ሂማኒቲ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ዶ/ር ካልፍ ሙባረክ፣ የሃይማኖቶች አባቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ በዚሁ ወቅት፤ የኃይማኖት ተቋማት የመቻቻል፣ አብሮ የመኖርና የመተሳሰብ እሴት በማጠናከረ ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያንም ብዝሃ ኃይማኖቶች በጋራ ተቻችለው የሚኖሩባት በመሆኑ ለዓለም ትልቅ ምሳሌ እንደሆነች አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት ዓለም ላይ የፅንፈኝነትና የመከፋፈል ሀሳብ አብሮ ለመኖር አደጋ እየሆነ መምጣቱ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

ኃይማኖት ተቋማት ለአብሮነትና መቻቻል አደጋ የሆነው የፅንፈኝነትና የመከፋፈል ሀሳብ ለማስወገድ በቁርጠኝነት መስራት አለባቸው ብለዋል።

በጉባኤው የኃይማኖት ተቋማት ሀገራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩበት፣ የጋራ ተግዳሮቶችን  በጋራ ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት መምከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የሠላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም በበኩላቸው የሃይማኖት ተቋማት ሰላምን በማስፈን ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል።

አሁን ላይ በዓለም ላይ  እያጋጠሙ ያሉ የመከፋፈል ችግሮች ለመፍታት የኃይማኖት ተቋማት የመቻቻል ትርክትን  መገንባት ላይ መስራት አለባቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የኃይማኖት መሪዎች እና ተቋማት በተለያዩ እምነቶች መካከል ውይይት እና መግባባትን መፍጠር፣ የተዛባ አመለካከትን ማረም እና መከባበርን ማጎልበት ላይ አበክረ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top