የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የቅደመ ማስጠንቀቂያ ስርዓትን ማጎልበት ይገባል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

2 Days Ago 85
የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የቅደመ ማስጠንቀቂያ ስርዓትን ማጎልበት ይገባል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና ጠንካራ የውሃ ሀብት አስተዳደር ለመገንባት የቅደመ ማስጠንቀቂያ ስርዓትን ማጎልበት ያስፈልጋል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ፡፡  

ዓለምአቀፍ የሃድሮሜት ኮንፈረንስ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት እየተካሄደ ነው፡፡

ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ እየተፈተነች መሆኑን ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ዋነኛ የችግሩ ተጠቂዎች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ከምጣኔ ሀብት ተጽዕኖው ባሻገር የበርካቶችን ህይወት እየቀጠፈ መሆኑን በማንሳትም ዘመኑን የዋጀ የጋራ መፍትሔ ማዘጋጀት ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ባለፉት 6 ዓመታት 40 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን የጠቀሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ችግሩን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች እና ለጎረቤት አገራት ዘላቂ ልማት እና ብልጽግና ጭምር አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና ጠንካራ የውሃ ሀብት አስተዳደር ለመገንባት የቅደመ ማስጠንቀቂያ ስርዓትን ማጎልበት እንዲሁም የመረጃ ልውውጥን ማጠናከር ላይ አገራት በትብብር መስራት አለባቸው ብለዋል፡፡

ይህም ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት ብቻ ሳይሆን ቀድሞ ለመከላከል ይረዳል ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ በርካታ ፈተናዎች እንደገጠሟት የጠቆሙት የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ፤ በኮንፈረንሱ የኢትዮጵያ ተሞክሮ እንደሚቀርብ እና የልምድ ልውውጦች እንደሚደረጉ ተናግረዋል።

በኮንፈረንሱ የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ፕሬዝዳንት አብዱላ አህመድ ማንዱስን ጨምሮ የተለያዩ አገራት ተወካዮች እና የዘርፉ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።

በአሸናፊ እንዳለ

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top