"የቁልፍ መሠረተ ልማት ደህንነት ለዲጂታል ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ቃል ላለፉት ሦስት ሳምንታት ሲካሄድ የቆየው 5ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር የማጠቃለያ መርሐ ግብር በድሬዳዋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ፤ የሳይበር ደህንነት እና የዲጂታል መታወቂያ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ጉዞ ወሳኝ መሆኑን በመርሐ ግብሩ አንስተዋል።
የዲጂታል መታወቂያ የማንነትን መረጃን በመያዝ ወንጀልን ለመከላከል የሚኖረው ሚና የማይተካ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ለዚህም ስለ ዲጂታል መታወቂያ ለዜጎች ግንዛቤ በመስጠትና አገልግሎቶችን ከዲጂታል መታወቂያ ጋር ማስተሳሰር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በሳይበር ላይ የሚሰነዘር ጥቃት በሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ፣ ከዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ጎን ለጎን ለሳይበር ደህንነት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝም ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር በበኩላቸው፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በፈጠራና በክህሎት ላይ የተመሰረተ ኢንዲሆን ያስችላል ብለዋል።
መድረኩ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነትን በመፍጠር በድሬዳዋ አስተዳደር ቀልጣፋ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ስማርት ከተማ ለመፍጠር የሚደረገውን ጉዞ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
በመርሐ ግብሩ "በዲጂታል ኢኮኖሚ ጉዞ የሳይበር ደህንነትና የዲጂታል መታወቂያ ሚና" በሚል ርዕስ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።