በጋምቤላ ክልል ነገ የሚከበረውን የሰንደቅ አላማ ቀን ምክንያት በማድረግ "የሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ ለሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችን እና ለሉዓላዊነታችን ዋስትና ነው" በሚል መሪ ቃል ዕለቱ በፓናል ውይይት መከበር ጀምሯል።
የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ባንቺአየሁ ንገታ በአሉን በየአመቱ ማክበር ያስፈለገው ዜጎች ስለ ሰንደቅ አላማ ምንነት ክብር እና ትርጓሜ በተገቢው መንገድ ተረድተው ስለ ሀገራቸው ሉዓላዊነት እና ነፃነት በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል ነው ብለዋል።
ዜጎች ለሰንደቅ አላማ የተደረገውን ተጋድሎ በአግባቡ በመረዳት የጋራ መግባባት እና ህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነትን ለማፅናት የድርሻቸውን እንዲወጡ የበአሉ መከበር ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ዋና አፈጉባኤዋ ተናግረዋል።
በአሉን ስናከብር ሰላማችንን በማስጠበቅ አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል የገባነውን ቃል በማደስ በጋራ መስራት እንደሚገባ ወይዘሮ ባንቺአየሁ በፓናል ውይይቱ ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል ።
በፓናል ውይይቱ ላይ የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ቴንኳይ ጆክን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የመንግስት ሰራተኞች እና የተለያዩ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።
በሚፍታህ አብዱልቃድር