የፌዴራሉ መንግስት 12ኛ ክልል ሆኖ የሚመሰረተው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሕገ-መንግስትና ሰንደቅ ዓላማ በአብላጫ ድምጽ ፀደቀ።
አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ህገ-መንግስት አጽዳቂ ኮሚሽን በዛሬው ዕለት በአርባ ምንጭ ከተማ ጉባኤ አካሂዷል።
በጉባዔው ላይ ህገ-መንግስቱ ስለያዛቸውና አጠቃላይ በህግ ማዕቀፉ ዙሪያ የደቡብ ክልል ፍትህ ቢሮ ዐቃቤ ህግ ወንድማገኝ አበበ ገለጻና ማብራሪያ አድርገዋል።
በእዚህ መሠረት ህገ-መንግስቱ የህዝቡን ባህል፣ ታሪክና መልክአ ምድራዊ አሰፋፈር እንዲሁም የስነ-ልቦና አንድነት፣ የጋራ ጥቅምና መልማትን የሚያረጋግጥ ሆኖ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።
ህገ-መንግስቱ በክልሉ መልካም አስተዳርን በማስፈን የአገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም በእኩልነትና በፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ አሠራር እውን በማድረግ በኩል ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረውም አመልክተዋል።
ዐቃቤ ህግ ወንድማገኝ እንደገለጹት ህገ መንግስቱ 140 አንቀጾችን ይዟል።
በውስጡም በመሠረታዊ መርሆዎች የህዝብ ሉዐላዊነት፣ የህገ-መንግስት የበላይነት፣ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች፣ የመንግስትና የሃይማኖት መለያየት እንዲሁም የመንግስት አሠራርና ተጠያቂነት በማያሻማ መልክ መቀመጣቸውን አስረድተዋል።
በቀረበው ረቂቅ ህገ-መንግስት ላይ 167 የአጽዳቂ ኮሚሽን አባላት በስፋት ውይይት አድርገዋል።
የክልሉ መንግስት የሥራ ቋንቋ አማርኛ ሲሆን፣ በክልሉ የሚገኙ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በየምክር ቤቶቻቸው የየራሳቸውን የሥራ ቋንቋ ሊወስኑ እንደሚችሉም በህገ-መንግስቱ ተመላክቷል።
ህገ-መንግስቱ በ155 ድጋፍ፣ በ10 ተቃውሞ እና በሁለት ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።
በጉባኤው ላይ የክልሉ ሰንደቅ ዓላማና አርማ በሙሉ ድምጽ መፅደቁን ኢዜአ ዘግቧል።
በጉባዔው ላይ የህ-መንግስት አጽዳቂ ኮሚሽን፣ የፌዴራል፣ የክልልና የዞን እንዲሁም የልዩ ወረዳ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።