መመሪያ ያማረረው በፍ/ቤት ያስመርምረው

1 ዓመት በፊት 848
መመሪያ ያማረረው በፍ/ቤት ያስመርምረው

አንዳንድ ጊዜ መመሪያ መማረሪያ ሲሆን ይታያል። በነገራችን ላይ መመሪያ ማለት በደረጃው ከአዋጅ ቀጥሎ ያለ በፌደራል ወይም ለፌደራል መንግስት ተጠሪ በሆኑት በአዲስ አበባና በድሬደዋ ከተማ መስተዳድሮች የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በሚያወጣቸው አዋጆች በተሰጠው ከፊል የሕግ አውጪነት ስልጣን መሰረት አስፈፃሚው ወይም ሚኒስቴር፣ ኮሚሽን፣ ባለስልጣን፣ ኤጀንሲ፣ አገልግሎት፣ ኢንስቲትዩት፣ አስተዳደር፣ ጽ/ቤት ወይም ቢሮ የተሰኘ የመንግስት የአስተዳደር መ/ቤት የሚያወጣው አዲስ ወይም ነባሩን መመሪያ የሚያሻሽል ወይም የሚሽር የሕግ ሰነድ ነው። 

መመሪያ በሕግ የሚመራ እና የሚገዛ ካልሆነ በሰዎች መብቶች እና ጥቅሞች ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ስለሚኖረው መማረሪያ ይሆናል። 

በተለይ አንዳንድ መመሪያዎች የዕለት ተለት ሕይወታችን ላይ ባንድም ሆነ በሌላ መልኩ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ተፅእኖ የሚያሳርፉ ናቸው። ለምሳሌ በቅርቡ በስራ ላይ ከዋሉ መመሪያዎች መካከል የቤት ኪራይ ጭማሪ ክልከላ፣ የፍጆታ እቃዎችን የዋጋ ተመን፣ የነዳጅ ግብይት እና ዋጋ ተመንን የሚመለከቱ መመሪያዎች ይጠቀሳሉ። 

እነኚህ መመሪያዎች ቅር ያሰኙት ባለጉዳይ ታዲያ ሕጋዊነታቸው ገለልተኛ በሆነ ዳኝነት ካልታየለት ተቋሙም "መመሪያ መመሪያ ነው ሲል!?" ባለጉዳዩም "የፍትህ ያለህ!" እያለ አስተዳደራዊ ፍትህ ተነፍጎ ሲያማርር ሊኖር ነው። ይህን ችግር ለመፍታት ከብዙ ዓመታት ጥበቃ በኋላ አንድ ሕግ ወጥቷል። 

ይህ ሕግ የፌደራል የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 ይባላል። መጋቢት 24 ቀን 2012 ዓ.ም በነጋሪት ጋዜጣ ላይ ታትሞ ስራ ላይ ከዋለበት ቀን ጀምሮ ሦስት ዓመት ከአምስት ወራትን አስቆጥሯል። ምን ያህሎቻችን ስለዚህ አዋጅ አውቀን ተጠቅመንበት ይሆን? 

ይህ አዋጅ የማይመለከታቸው የዐቃቢ ሕግ፣ የፖሊስ፣ የመከላከያ እና የደህንነት ተቋማት ብቻ ናቸው። እንዲሁም ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ እና የወለድ ተመንን ወይም ተመሳሳይ ምስጢራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የመመሪያ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓትን ለመከተል አይገደድም። እነኚህ ተቋማትም ቢሆኑ ግን ከመደበኛ ኃላፊነታቸው ጎን ከሚሰጡት አገልግሎትና ከሚያከናውኑት የቁጥጥር ስራ ጋር በተያያዘ አዋጁ ይመለከታቸዋል። ሌሎች የፌደራል፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ተቋማት ግን ከገቢዎችና ጉምሩክ እስከ መሬት አስተዳደር፣ ጤና፣ ንግድ፣ የነዋሪዎች አገልግሎት፣ ወዘተ ጋር በተገናኘ በየደረጃው የሚያወጧቸው መመሪያዎች በአዋጁ መሰረት መሆን አለባቸው። 

መመሪያ እስኪወጣ በሚል ምክንያት የእርስዎ ጉዳይ መጓተት የለበትም። የጠቀስናቸው የመንግሥት አስተዳደር ተቋማት ስልጣኑን የሰጣቸው ሕግ ላይ አስገዳጅ ከሆነ ሕጉ በወጣ በሦስት ወር ውስጥ ካልሆነ ደግሞ በተገቢው ጊዜ መሆን አለበት። እንደ አንድ ግለሰብ መመሪያው አለመውጣቱ መብቶን የሚነካ ከሆነ ሚኒስቴር መ/ቤትም ሆነ ባለሥልጣን፣ የአዲስ አበባም ሆነ የድሬዳዋ ቢሮ፣ ፅ/ቤት፣ አስተዳደር፣ መ/ቤት መመሪያውን እንዲያወጣ ሊጠይቁት፣ ፍቃደኛ ካልሆነም በፍ/ቤት ሊያስገድዱት ይችላሉ። 

ማንኛውም ባለጉዳይ በተቀመጠው ጊዜ መመሪያ ያላወጣውን መ/ቤት እንዲያወጣ በፅሁፍ መጠየቅ፣ መ/ቤቱም በ30 ቀናት ውስጥ ማውጣት ወይም ያልቻለበትን ምክንያት ለባለጉዳዩ ማሳወቅ አለበት። 

መመሪያ ዝም ብሎ ከኪስ አይወጣም። የሚያወጣው ተቋም በሂደት ላይ ያለ መመሪያን ረቂቅ ርእሰ ጉዳይ፣ የአወጣጡን መርሐ-ግብር፣ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ፣ ረቂቅ መመሪያውን በተመለከተ ያሳተማቸውን ማስታወቂያዎችና የተሰበሰቡ አስተያየቶችን እና ተቋሙ ባስተያየቶቹ ላይ የወሰደውን አቋም የሚያሳይ መዝገብ ማደራጀት እና ለማንኛውም ሰው ተደራሽ እንዲሆን ማመቻቸት አለበት። 

አስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ከሌለ ወይም መመሪያውን ማሳወቁ የሕዝብን ጥቅም የሚጎዳ ወይም መመሪያውን ፋይዳ የሚያሳጣው ካልሆነ በቀር ተቋሙ መመሪያውን ከማውጣቱ በፊት ሰፊ ስርጭት ባለው ጋዜጣ፣ በተቋሙ ድረገፅ እና በሌሎች መገናኛ ብዙሀን ጭምር መሰረታዊ የመመሪያውን መረጃ ቅጂውን ማግኘት ስለመቻሉ እና ማንኛውም ሰው የፅሁፍ አስተያየት ወይም ሀሳብ የሚሰጥበት መድረክ መቼና እንዴት እንደሆነ ማሳወቅ አለበት። ቢያንስ የ15 ቀን ጊዜ ሰጥቶ ከሚመለከታቸው አካላት እና ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስተያየት መጠየቅ፣ የፅሁፍ አስተያየት መቀበያ ጊዜው ካበቃ በኋላ ሕዝቡ እንዲወያይበት እና አስተያየት እንዲሰጥበት መድረክ ማዘጋጀት አለበት።  የሰበሰበውን የሕዝብ አስተያየት ማካተት፣ የማያካትት ከሆነ ምክንያቱን የሚያብራራ ፅሁፍ ማዘጋጀት ያለበት ሲሆን፤ ሕዝብ የመከረበትን ረቂቁን መመሪያ በጉልህ መለወጥ ወይም አዳዲስ ግዴታዎችን በተገልጋዩ ላይ ማካተት አይኖርበትም። 

ማንኛውም መመሪያ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መመዝገብ አለበት። ተቋሙም ያወጣውን መመሪያ በድረ ገፁ ላይ መጫን፣ አሳትሞ ለሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ማሰራጨት እና ለማንኛውም ለሚፈልግ ሰው ባለበት እንዲመለከት ወይም በራሱ ወጪ ኮፒ አድርጎ እንዲወስድ መፍቀድ አለበት። የተደበቀ፣ ያልተመዘገበና በተቋሙ ድረ ገፅ ላይ ያልተጫነ መመሪያ ተፈፃሚነት አይኖረውም። 

አንዳንድ ተቋማት ባለጉዳይ እየመረጡ ከመሳቢያቸው የደበቁትን መመሪያ አውጥተው የሚያስተናግዱበትን፣ ላልተመቻቸው ደግሞ መመሪያ የለም፣ መመሪያው አይፈቅድም የሚሉበትን ተግባር ለመከላከል ነው ሕዝብን የማወያየት፣ ተደራሽ የማድረግ ግዴታን አለመወጣት መመሪያውን ውጤት አልባ የማድረግ ጉልበት የተሰጠው። 

ይህን ዓይነት መመሪያ ያወጣ ተቋም መመሪያው ሕጋዊ ተፈፃሚነት እንዲኖረው የተጠቀሱትን የመመሪያ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓቶች ጠብቆ መመሪያውን እንደ አዲስ ከማውጣት ውጭ ሕገ ወጥ መመሪያ ሕዝቡ ላይ መጫን አይችልም። 

ይህ ዓይነቱ መመሪያ ጥቅሙን ወይም መብቱን የነካበት ማንኛውም ባለጉዳይ ለአስተዳደር ተቋሙ እስከ መጨረሻው የውሳኔ አካል ቅሬታውን አቅርቦ አጥጋቢ ምላሽ ካላገኘ መመሪያው ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ በ90 ቀናት ውስጥ መመሪያው እንዲከለስ ለፌ/ከ/ፍ/ቤት ማቅረብ ይችላል። ተቋሙ ያወጣው መመሪያ ከሥልጣኑ በላይ ከሆነ፣ ወይም ከአዋጅ ወይም ከበላይ ሕግ የሚቃረን ከሆነ ደግሞ በማንኛውም ጊዜ ለፍ/ቤት መመሪያው እንዲከለስ አቤቱታ ማቅረብ ይችላል። 

ስለዚህ "መመሪያ ነው!" የሚባል ምላሽ ብቻ በቂ አይደለም። መመሪያው መብቱን የነካበት ማንኛውም ሰው ሕጋዊነቱን ፍ/ቤት እንዲያይለት በሚያቀርበው ጥያቄ መሰረት ፍ/ቤቱ መመሪያው የወጣበትን አግባብ መርምሮ የጠቀስናቸውን የሕጋዊ መመሪያ አወጣጥ ሥርዓት ካልተከተለ ተገቢውን ውሳኔ ይሰጥበታል። የአስተዳደር መ/ቤት በጉዳያችሁ ላይ የሚወስነው ውሳኔም "ተወስኗል!" ተብሎ "ምን ይደረግ!?" የሚባል አይደለም። በፍ/ቤት ይፈተሻል ይከለሳል። ለዚህ ጉዳይ ሳምንት ቀጠሮ እንያዝለት።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top