መንግሥት ትግራይ ክልልን ጨምሮ በሁሉም የhገሪቱ አካባቢዎች የቅድሚያ ቅድሚያ የምግብ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የምግብ እርዳታን ተደራሽ የማድረግ ስራ መጀመሩን ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገለፀ።
የአዳማ የእርዳታ ማስተባበሪያ ማዕከልን ጨምሮ ከስምንት ማዕከላት አልሚ ምግቦችን ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የማጓጓዝ ስራ ዛሬ ተጀምሯል።
በብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የሎጄስቲክስ ኦፕሬሽን ዘርፍ ሥራ አመራር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተዎድሮስ ደምሴ በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት፥ የተለያዩ አጋር ድርጅቶች ሰብዓዊ ዕርዳታ ላልተገባ ዓላማ ውሏል በማለት ባለፉት ሶስት ወራት የሚያደርጉትን ድጋፍ ማቆማቸውን ገልጸዋል።
መንግሥት ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በመጠለያ ያሉትን ወገኖች ጨምሮ በሰው ሰራሽ እና ድርቅን ጨምሮ በተፈጥሮ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የትግራይ ክልልን ጨምሮ በ12ቱም የሀገሪቱ ክልሎች ቅድሚያ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ድጋፍ የማድረስ ስራ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህም በዛሬው ዕለት ከ115 ሺህ ኩንታል በላይ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ዳቦና የበቆሎ ዱቄት እንዲሁም ለእናቶችና ህፃናት የሚውል አልሚ ምግብ ተደራሽ የማድረግ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።
አዳማ ከሚገኘው ትልቁ ማከማቻ መጋዘን፣ ከሆረታ፣ ከሽንሌ፣ ከድሬዳዋ፣ ከወላይታ ሶዶ እና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከሚገኙ የኮሚሽኑ ማዕከላት ሰብዓዊ ዕርዳታ የማጓጓዝ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።
መንግሥት በቀጥታ ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ ህዝቡ እየተጋጋዘ መሆኑን በመግለጽ፤ በተለይም የምግብ ክፍተት ባለባቸው አካባቢዎች ያሉ ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ 4 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
በሰብዓዊ ድጋፍ ስርጭት ላይ በለጋሽ ድርጅቶች የቀረበውን ቅሬታ በተመለከተ መንግሥትና ኮሚሽኑ በተቀናጀ መልኩ የምርመራና የማጥራት ስራ እየሰሩ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ 24 ትላልቅ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ የሰብዓዊ ድጋፍ ክምችቶችን በየጊዜው ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ የገለፁት ደግሞ በኮሚሽኑ የአዳማ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ወንድወሰን ፍቃዱ ናቸው።
በተለይም ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሲከሰቱ በሚቀርበው ጥያቄ መሰረት ኮሚሽኑ ስርጭቱን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በዛሬው ዕለት 50 የሚደርሱ ተሽከርካሪዎች ሰብዓዊ ድጋፉን ወደ ተለያዩ አካባቢዎች እያጓጓዙ ይገኛሉ ብለዋል።
የምግብ ዘይት፣ ጥሬ ስንዴና በቆሎ፣ ሩዝና አልሚ ምግቦች ከማዕከሉ ተጭነው ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ተደራሽ እየተደረጉ መሆኑንም አቶ ወንድወሰን ገልጸዋል።