"አሁን ላይ በልዩ ኃይል የሚታዘዝ አደረጃጀት እና የኮማንድ ሥርዓት ያለው ክልል የለም"- ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ

1 Yr Ago 1879
"አሁን ላይ በልዩ ኃይል የሚታዘዝ አደረጃጀት እና የኮማንድ ሥርዓት ያለው ክልል የለም"- ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ

የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ አሁን ላይ በልዩ ኃይል የሚታዘዝ አደረጃጀት እና የኮማንድ ሥርዓት ያለው ክልል አለመኖሩን እና እነዚህ ኃይሎች ወደ መከላከያ፣ ፌዴራል ፖሊስ እና መደበኛ ፖሊስ መቀላቀላቸውን ገለጹ።

በትግራይ ክልልም መደበኛ ፖሊስ እና ሚሊሻ ብቻ እንደሚኖር ጠቅሰው፣  ትጥቅ የማስረከብ ሥርዓቱ መጀመሩን እና በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።

ጄኔራሉ  በየሦስት ወሩ ከሚታተመው መከታ መጽሔት ጋር የልዩ ኃይሎችን አደረጃጀት በተመለከተ ቃለ-ምልልስ አድርገዋል።

በአገሪቱ የነበሩት ልዩ ኃይሎች እና ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ሕገ-መንግሥቱ ከሚፈቅደው አግባብ ውጪ የተደራጁ እንደነበሩ የጠቀሱት ጀኔራሉ፣ ሕገ መንግሥቱ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ውጪ በየክልሉ እንዲኖሩ የሚፈቅደው ፖሊስን እና ሚሊሻን ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።

ይሁንና ባለፉት ጊዜያት ክልሎች በወታደራዊ ቁመናቸው እና ትጥቃቸው የዘመኑ እና በሰው ኃይላቸው የገዘፉ ልዩ ኃይሎችን ገንብተው መቆየታቸውን ነው የገለጹት።

ከለውጡ በኋላም ይህንን ልዩ ኃይል መልክ ለማስያዝ በመንግሥትም በሕዝቡም በኩል ፍላጎት እንደነበር ጠቅሰዋል።

በየክልሉ ያሉ ልዩ ኃይሎች ወታደራዊ ጡንቻቸውን እያፈረጠሙ መሔዳቸው እና ትጥቅ በኢ-መደበኛነት በተደራጁ ኃይሎች እጅ በብዛት መግባቱ ስጋት ያሳደረባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችም መንግሥት ይህንን ጉዳይ መልክ ያስይዘው ዘንድ ሲጠየቁ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

የነበረውን አደረጃጀት ወደ ሥርዓት ለመመለስ፣ እነዚህን ኃይሎች እንደ ኃይል ሪፎርም ለማድረግ እና መልሶ ለማደራጀት በተደረገው ጥናት መሠረት  በሀገር ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ እና የሌሎች ሀገሮችን ልምድ እና ተሞክሮ መውሰድ እንደተቻለ ጠቁመዋል።

ሕገ-መንግሥቱ በሚያዘው መሠረት በልዩ ኃይል እና ኢ-መደበኛ የተደራጁ ኃይሎች የሀገሪቱ አቅም እንዲሆኑ እና አባላቱም የኑሮ ዋስትና እንዲኖራቸው ወደ ፀጥታ ኃይሉ ገብተው እንዲደራጁ ጠነካራ አቋም መያዙን ገልጸዋል።

መንግሥት እና መከላከያ ለሀገር አስተዋፅኦ ያደረጉ እና በፀጥታ ማስከበር ሥራ ላይ ተሰማርቶ የቆየ አንድም ግለሰብ ቢሆን ከሥራ ውጪ መሆን የለበትም የሚል አቅጣጫ ይዘው መሥራታቸውን ነው የተናገሩት።

በዕድሜ መግፋት፣ በሕመም እና ከፍ ያለ ጉዳት ደርሶባቸው መሥራት የማይችሉትን ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው፤  መልሶ መቋቋም የሚያስፈልጋቸውም በተሐድሶ ኮሚሽን ከሚቋቋሙት ጋር እንዲቋቋሙ በሚል ወደ ሥራ መገባቱን ጠቅሰዋል።

ይሁንና ሂደቱ እንዲስተጓጎል ፅንፈኛው ኃይል ያካሄደው አፍራሽ ቅስቀሳ ብዙ ነበርያሉት ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ "የሌላው ክልል ትጥቅ ሳይፈታ አንተን ብቻ ነው የሚያስፈቱት" የሚል የፅንፈኛ ፕሮፓጋንዳ በስፋት እንደነበር ተናግረዋል።

ፅንፈኞች እና ሥልጣንን ሕገ-መንግሥቱ ከሚፈቅደው ውጪ መያዝ የሚፈልጉ ወገኖች ይሄንን ኃይል እንደ ኃይል እንዲቀጥል ይፈልጋሉ ብለዋል።

ይህም በብሔር ስም የተቋቋሙ የታጠቁ አደረጃጀቶችን በብሔር አጀንዳ እየቀሰቀሱ በነውጥ ሥልጣን መያዣ ሊያደርጓቸው ስለሚያስቡ ነው ብለዋል።

ተጨባጩ ዕውነታ ግን ሁሉም ክልሎች በዚህ ፕሮግራም ውስጥ የታቀፉ መሆናቸው እና ያልታቀፈ ክልል አለመኖሩ ነው ብለዋል ጄኔራል አበባው።

ይሄ መሆኑ እየታወቀ ለተወሰነ ክልል ብቻ የመጣ ተደርጎ በየሚዲያው ፕሮፓጋንዳው ቀድሞ ስለተሠራጨ እና ብዥታ ስለፈጠረ በአማራ አካባቢ  የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ችግር ተፈጥሯልም ሲሉ ገልጸዋል።

ሠራዊቱ በለመደው አሠራር ሕዝባዊ ወገኝተኝነቱን መሠረት አድርጎ በውይይት ለማስተካከል ተሞክሮ ስኬታማ ሆኗል፤ አሁን ሁሉም ወደ ተቀመጠላቸው አደረጃጀታቸው እንዲገቡ ተደርገዋል ብለዋል።

የትግራይ ክልል ኃይልን በተመለከተ እንደ ማንኛውም ክልል በክልሉ የሚኖረው መደበኛ ፖሊስ እና ሚሊሻ ብቻ ነው የሚኖረው ብለው፣ በተቀመጠለት ስታንዳርድ ትጥቅ የማስረከብ ሥርዓቱ የተጀመረ ስለሆነ በቅርቡ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በጦርነት የተፈጠረውን የፋኖ ኃይል ወደ ሕገ-ወጥ አሰላለፍ አስገብተው ሊጠቀሙበት የሚፈልጉ ፅንፈኞች ወደ ሕጋዊ አሠራር እንዳይገባ ከፍተኛ ቅስቀሳ አድርገው እንደነበር ተናግረዋል።

መንግሥት ግን የፋኖን ኃይልም ለሀገር የሚጠቅም ኃይል ነው፤ በጦርነት ጊዜ የከተተ ነው፤ ይህ ኃይልም ልክ እንደ ልዩ ኃይሉ አማራጭ ይሰጠው በሚል በመደበኛ ፖሊስ እና በመከላከያ አማራጭ እንደተቀመጠ እና በተሳካ መንገድም እንደተፈጸመ ነው የገለጹት።

መንግሥት ያስቀመጠውን ወደ ሕጋዊነት የማስገባት ፕሮግራም አልቀበልም ብለው የኃይል አማራጭ ከተከተሉት ጋር ችግሩን በሁለት መንገድ  ለመፍታት መሞከሩን ጠቅሰዋል።

የመጀመሪያው ፕሮግራሙ ምን እንደሆነ ለፋኖው እንዴት እንደሚጠቅመው በማስረዳት እና በማወያየት ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ገልጸው፣ አብዛኛዎቹ ወደ ተፈለገው መስመር መግባታቸውን ገልጸዋል።

"አሻፈረኝ ብሎ የአመፅ መንገድን የመረጠውን ግን ሕጋዊው አሠራር የግድ ተግባራዊ መደረግ ስለነበረበት በመረጠው መንገድ ሄደን መስመር አስይዘነዋል" ብለዋል ጄኔራሉ።

ጄኔራል አበባው የዚህን ሀገራዊ ወታደራዊ አቅምን የማጠናከር እና የፀጥታ ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ አደረጃጀቶችን ወደ ሕጋዊነት የማስገባት አሠራር ለማደናቀፍ የሚሠሩ ኃይሎች ከድርጊታቸው ቢታቀቡ መልካም ነው ብለዋል።

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top