እየተስተዋለ ያለው የግብረ-ገብ ጉድለት የአስተዳደግ መንገዳችንን በደንብ እንድናጤን የሚያደርግ ነው፡- የግብረ-ገብ መምህር ጠና ደዎ (ዶ/ር)

4 ወር በፊት 473
እየተስተዋለ ያለው የግብረ-ገብ ጉድለት የአስተዳደግ መንገዳችንን በደንብ እንድናጤን የሚያደርግ ነው፡- የግብረ-ገብ መምህር ጠና ደዎ (ዶ/ር)
በወጣቶች ዘንድ እየተስተዋለ ያለው የግብረ-ገብ ጉድለት የአስተዳደግ መንገዳችንን በደንብ እንድናጤን የሚያደርግ ነው ሲሉ የግብረ-ገብ መምህሩ ጠና ደዎ (ዶ/ር) ይገልጻሉ።
 
ከኢቢሲ ሳይበር ጋር ቆይታ ያደረጉት የግብረ-ገብ መምህሩ፤ የሥነ-ምግባር ጉድለት ሲታይ "ይሄ ትውልድ" የሚለው አባባል ልጆቻችንን በአግባቡ እንዳላስተማርን የሚያመላክት ነው በማለት፣ያላስተማርናቸውን እና ያላስተላለፍነውን ሥርዓት ከትውልዱ ልንጠብቅ አይገባም ሲሉ ይናገራሉ፡፡
 
ግብረ-ገብ መልካም እና መጥፎ እንዲሁም ጎጂ እና ጠቃሚ ነገሮችን የምንለይበት ነው ይላሉ፡፡
 
ይህ ሥብዕና በሥነ-ምግባር እንደሚጠና በማስታወስ ሰው የራሱን ችግር መታደግ እንዲችል አቅም ለመፍጠር ሲል የፈጠረው፣ሌሎች ደግሞ ከፈጣሪ የተሰጠ ነው ብለው እንደሚያምኑ ያስረዳሉ፡፡
 
በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን ባህሪ የሚያሳዩ ዜጎች ሲፈጠሩ፣ ሀገር ምስጉን ግብረ-ገብ ያላቸው ዜጎች አፍርታለች ለማለት እንችላለን ይላሉ መምህሩ።
 
አሁን ላይ እየተስተዋለ ያለው የግብረ-ገብ ጉድለት ይህን የሚያመላክት እንዳልሆነ በመግለጽ፤ የአስተዳደግ መንገዳችንን በደንብ ማጤን ያስፈልገናል ይላሉ።
 
ልጆች በነፃነት ይደጉ የሚለው የምዕራባውያን እሳቤ መልካም ቢሆንም፤ ነፃነቱን በምን መልኩ ይጠቀሙት የሚሉት ነጥቦች አብረው ልብ ሊባሉ እንደሚገባ ነው የሚገልጹት፡፡
 
ወላጆች መልካም እያስተማሩ፣ ጎረቤት መጥፎ ካስተማረ ፋይዳ እንደሌለው በመግለጽ፤ እንደ ማህበረሰብ ቅንጅት እንደሚያስፈልግ ያነሳሉ፡፡
 
አንድ ዜጋ ለሀገሩ እና ለወገኑ የማይመች መሆን የለበትም የሚሉት ግብረ-ገብ መምህሩ፤ ሀገሩን እና ወገኑን የማይጠብቅ በተለይ ብሔራዊ ኩራት ለሆኑ ተቋማት ዋጋ የማይሰጥ ዜጋ ማፍራታችን ሊያነቃን የሚገባ እና በግብረ-ገብ ዙሪያ ትኩረት ሰጥን መስራት እንዳለብን የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡
 
በአፎሚያ ክበበው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top