የደም ክምችት እጥረት በመከሰቱ ለጋሾች ደም እንዲሰጡ ጥሪ ቀረበ

11 Mons Ago
የደም ክምችት እጥረት በመከሰቱ ለጋሾች ደም እንዲሰጡ ጥሪ ቀረበ
የኢትዮጵያ ደም ባንክ የክምችት እጥረት ስላጋጠመው ለጋሾች ደም እንዲለግሱ የኢትዮጵያ የደምና ህብረ- ህዋስ ባንክ አገልግሎት ጥሪ አቅርቧል።
ባለፉት በክርስትና እና እስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በነበሩት የአጿማት ወቅቶች በቂ ደም ባለመለገሱ የደም ክምችት እጥረት መከሰቱን የኢትዮጵያ የደምና ህብረ- ህዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ታዬ ገልጸዋል፡፡
የአጿማቱን መጠናቀቅ ተከትሎ የደም ለጋሾች ቁጥር መሻሻል ያሳየ ቢሆንም አሁንም ካለው የደም ፍልጎት አንጻር እየተሰበሰበ ያለው ደም በቂ አለመሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በተለይ ለኢቢሲ ሳይበር ተናግረዋል፡፡
በተለይ የደም ተዋጽኦ ዝግጅቶች ላይ ጉድለቶች እንደነበሩ ጠቅሰው፤ ከዚህ ቀደምም ለጋሾ ች ደም እንዲለግሱ ጥሪ ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
እንደ ሀገር ባለፉት በዘጠኝ ወራት 250 ሺህ 235 ዩኒት ደም ማሰባሰብ መቻሉን የጠቀሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ፤ ታቅዶ የነበረው 343 ሺህ ዩኒት ደም ለማሰባሰብ የነበረ ሲሆን በዚህም አፈጻጸሙ 73 በመቶ በመሆኑ የፍላጎት እና የአቅርቦት አለመጣጣም እንደመሚያሳይ ተናግረዋል፡፡
በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያሉ ክልሎች ሙሉ በሙሉ ወደ ደም የማሰባሰቡ ስራ አለመግባታቸውም ለአፈጻጸሙ ጉድለት አንዱ ምክንያት ሆኖተጠቅሷል፡፡
በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የደም ማሰባሰቡ ስራ በጥሩ ደረጃ የሚገኝ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በደቡቡ የአገሪቱ ክፍል ያለው የደም ልገሳ ልማድ አነስተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የደም አሰባሰቡን የሚያስተጓጉሉ ወቅቶች እንዳሉ የጠቀሱት ኃላፊው፤ በተለይ በህዝባዊ በዓላት እና አጿማት ወቅት የደም ፍላጎት የሚጨምርበት ነገር ግን የደም ልገሳው የሚቀንስበት መሆኑና ተማሪዎች ፈተና እና እረፍት ላይ በሚሆኑበት ወቅትም በቂ ደም ማሰባሰብ እንደማይቻል አብራርተዋል፡፡
በሀገሪቱ የደም ልገሳ በሀል ሆኖ አንዲቀጥል የደም ለጋሾች ክለባትን የማጠናከር ስራዎች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ሀብታሙ፤ በአዲስ አበባ ብቻ 46 የደም ለጋሾች ክለባት መኖራቸውን ገልጸው ነገርግን አንዳንዶች በሚፈለገው ደረጃ እየተንቀሳቀሱ አለመሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
በደም እጥረት ምክንያት በርካታ ሰዎች የቀዶ ጥገና እንዲደረግላቸው እየጠበቁ በመሆኑን እና የህክምና ስርዓቱም ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል ሰፊ የሆነ የደም ለጋሾች ትብብር እንደሚያስፈለግ ተናግረዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ 43 የደም ባንኮች ሲኖሩ በተለያዩ ተቋማት ፣ ትቤ/ቶችና አደባባዮች ላይ በመንቀሳቀስ የደም ማሰባሰቡ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ሰኔ 7 ለሚከበረው የዓለም ደም ለጋሾች ቀንም የንቅናቄ ስራዎችን ለመስራት ዝግጅት እየተደረገ እንሚገኝም ነው የገለጹት፡፡
በማስተዋል መታፈሪያ

ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top