ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ፕሮጀክቶች ላይ የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገቧ ተገለፀ

15 Hrs Ago 67
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ፕሮጀክቶች ላይ የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገቧ ተገለፀ

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ፕሮጀክቶች ላይ የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገቧን የኢኒሼቲቩ ፕሮጀክቶች ሰብሳቢና የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለፁ።

የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ቀጣናዊ ፕሮጀክቶች አፈጻጸምን የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በጋራ ገምግመዋል።

የኢኒሼቲቩ ሰብሳቢና የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ጉዳዩን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ኢኒሼቲቩ በቀጣናው ሀገራት የመሰረተ ልማትና የሰው ሀብት ልማት፣ የግብርና፣ የጤና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂ  እንዲሁም አደጋዎች መከላከል ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

እነዚህ የቀጣናው የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና በጀት እንዲጠናቀቁ ክትትል የሚደረግ መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የቀጣናው የሰላምና የልማት ማዕከል በመሆኗ ኢኒሼቲቩ ውጤታማ እንዲሆን የማስተባበር ስራውን በትኩረት እየሰራች ትገኛለች ብለዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን በልማት ለማስተሳሰር የየሀገራቱ የገንዘብ ሚኒስትሮች ያቋቋሙት መሆኑንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ ለመልማት ካላት ፍላጎት አኳያ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን እየተገበረች መሆኑን ጠቅሰው፤ እስካሁን ከሶስት ቢሊዮን ዶላር በላይ የልማት ድጋፍ ማግኘቷን አመልክተዋል።

በተለይም በመንገድ፣ በባቡርና በሀይል መሰረተ ልማት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ለመተሳሰር የምታደርገው ጥረት ድጋፍ እንድታገኝ አስችሏል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በመጪው የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም የአፍሪካ ቀንድ የገንዘብ ሚኒስትሮችና አጋር አካላት በተገኙበት የኢኒሼቲቩ የፕሮጀክቶች አፈፃፀምና የአምስተኛ ዓመት ምስረታ መድረክ የሚካሄድ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ በዓለም ባንክ፣ በአውሮፓ ህብረትና፣ በአፍሪካ ልማት ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የተመሰረተ ቀጣናዊ የትብብር ማዕቀፍ ሲሆን ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቩን ታስተባብራለች።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top