አስደናቂ የተፈጥሮ ሀብቶችን የያዘው ማዜ ብሔራዊ ፓርክ

1 Mon Ago 541
አስደናቂ የተፈጥሮ ሀብቶችን የያዘው ማዜ ብሔራዊ ፓርክ

ማዜ ብሔራዊ ፓርክ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከአዲስ አበባ 468 ኪሎ ሜትር ርቀት ይገኛል። የክልሉ የፖለቲካ እና አስተዳደር ማዕከል ከሆነች ወላይታ ሶዶ ከተማ ደግሞ 83 ኪሎ ሜትር ይርቃል።

የማዜ ብሔራዊ ፓርክ ማዜ የሚለውን ስያሜውን ያገኘው በአከባቢው ከሚገኘው ማዜ ወንዝ ነው። ፓርኩ በጋሞ እና በጎፋ ዞኖች መካከል የሚገኝ ሲሆን ከሁለቱም ዞኖች የተለያዩ ቀበሌያትን ያወስናል። ፓርኩ ከ1997 ዓ.ም በፊት ጥብቅ ደን በማለት ጥበቃ ይደረግለት ነበር።

የማዜ ወንዝን ጨምሮ በፓርኩ ውስጥ የሚያልፉ በርካታ ወንዞች መድረሻቸው ኦሞ ወንዝ ነው፡፡ ማዜን ውበት ያጎናጸፉት እነዚህ ወንዞች ዳርቻቸው በደን የተሸፈነ ነው፡፡

በሳቫና ሳር የተሸፈነው ማዜ በተለይም ዝናብ በሚያገኝበት ወቅት ለምለምና አረንጓዴ መልክ የሚኖረው ሲሆን፣ ለእይታም በእጅጉ የሚስብ ነው፡፡ ማዜን የተለየ ከሚያደርጉት መገለጫዎች አንዱ በውስጡ የሚኖሩ የዱር እንስሳትን በቀላሉ የሚመለከቱበት ፓርክ መሆኑ ነው፡፡

የማዜ ሦስት ዓይነት የአየር ንብረት አለው፡፡ ቀዝቃዛ የሚሆንበት ወቅት ከሰኔ እስከ ነሐሴ ያለው ሲሆን፣ ከመጋቢት እስከ መስከረም ደግሞ ዝናብ የሚያገኝበት ወቅት ነው፡፡ ከህዳር እስከ የካቲት ያለው ወቅት ግን ሞቃታማ ወቅቱ ነው፡፡ በየዓመቱ 800 ሚሊ ሜትር ገደማ ዝናብ ያገኛል።

በ1997 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፓርክ መሰረታዊ መስፈርቶችን በማሟላት "ማዜ ብሔራዊ ፓርክ" በመባል ህጋዊ ከለላ እና ጥበቃ አግኝቷል።

የስዋይንስ ቆርኪ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ ሲሆን ይህ ዱር እንስሳ በማዜ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ መገኘቱ ፓርኩ ብሔራዊ እንዲሆን ካደረጉት መስፈርቶች ይጠቀሳል። ወደ 39 የሚሆኑ ከትንሽ እስከ ትልቅ አጥቢ የዱር እንስሳት በፓርኩ ወስጥ ይገኛሉ።

ጎሽ፣ ከርከሮ፣ የዱር አሳማ፣ ትልቁ አጋዘን፣ ዝንጀሮ፣ ጦጣ፣ ፌቆ፣ ቦሆር፣ ድኩላ፣ አንበሳ፣ አቦሸማኔ በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ ዱር እንስሳት ናቸው። የተለያዩ የዕፅዋት እና የአዕዋፋት ዝሪያዎችም ይገኙበታል።

202 ስኩዌር ኪሎሜትር ስፋት ያለው ፓርኩ በሰንሰለታማ እና በድንቅ አፈጣጠር የተዘረጉ ተራራዎች የከበቡት እና በርካታ አስደናቂ መስህቦችን አቅፎ የያዘ ነው፡፡ ቢልቦ ወይም ሀቦ የተፈጥሮ ፍል ውሃ በማዜ የላይኛው ተፋሰስ የሚገኝ ሲሆን በፋዋሽነቱም ይታወቃል፡፡

ወንጂያ ትክል ድንጋይ ዋሻ ከ300 ያላነሰ ህዝብ መያዝ የሚችል ዋሻ ሲሆን ማዜ ከያዛቸው መዳረሻዎች መካከል አንዱ መስህብ ነው፡፡

ብሔራዊ ፓርኩ ለተፈጥሮ አፍቃሪዎች እና ለዱር እንስሳት አድናቂዎች መዳረሻ የሚሆን ውብ የኢትዮጵያ ሀብት ነው፡፡

በትዕግስቱ ቡቼ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top